Sunday, September 22, 2024
spot_img

አሜሪካ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የጦር መሣሪያ ግዥ እገዳ መጣሏን በይፋ አሳወቀች

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 23 2014 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የጦር መሳሪያ እና የጦር ቴክኖሎጂ ግዥ እገዳ ማድረጉን በይፋ አሳውቋል፡፡ አገሪቱ እገዳውን የጣለችው ከትግራይ ጦርነት ጋር በተገናኘ መሆኑ ነው የተጠቀሰው፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የጣለችው ማእቀብ በትላንትናው እለት ከጀመረው የፈረንጆቹ ኅዳር አንስቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ የአሜሪካ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ዲፓርትመንት አሳውቋል፡፡

አገሪቱ በትግራይ የሚካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ባለፈው ግንቦት ወር በተመሳሳይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ የደህንነት ድጋፍ ማዕቀብ ጥላ የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱ እና ተከትሎት የመጣው ቀውስ ተባብሷል በማለት ሁለቱም አገራት ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ እንዳይገዙ የሚደነግገውን ማእቀብ ይፋ አድርጋለች፡፡   

አሜሪካ የጣለችው ማዕቀብ ኢትዮጵያ እና ኤርትራን ከማንኛውም በአሜሪካ ውስጥ ከሚገኝ አምራች እና የንግድ ተቋም የጦር መሳሪያና የጦር ቴክኖሎጂ ግዥ እንዳይፈፅሙ የሚከለክል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም አገራት የሚገኙ ሌሎች በሥም ያልተጠቀሱ ኃይሎችም በእገዳው ተካተዋል፡፡

በነገው እለት ጥቅምት 24፣ 2014 ከተጀመረ አንድ ዓመት የሚደፍነው በትግራይ ክልል የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት፣ አሁን የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀብ የጣለችው አሜሪካ፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ እቀባ መጣሏ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመስከረም ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት በትግራይ ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸውም አይዘነጋም፡፡

ይህ ማዕቀብ የኢትዮጵያን ፌዴራል መንግሥት፣ በጦርነቱ ተሳትፎ ባደረገችው የጎረቤት ኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደር እና የሕወሓት አባላትን ተጠያቂ የሚያደርግ እንደሆነም ተገልጾ ነበር፡፡ ይህን የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ በዋነኝነት ያስፈጽማል የተባለው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሲሆን፣ አሁን የጦር መሳሪያ ግዥ እግድ የጣለው የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱት ተባባሪ ይሆናል ተብሎ ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

1 COMMENT

  1. ምንጭ የለም። ትናንት የሰራችሁት ቢልለኔ ስዩም ከህወሓት ጋር ድርድር ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ ሰጡ የሚለው ዜናም እንዲሁ ለማረጋገጥ አዳጋች ሆኗል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img