አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 22፣ 2014 ― የትምህርት ሚኒስቴር መቀሌ እና አክሱምን ጨምሮ በ5 ዩኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ የነበሩ መምህራንን በጊዜያዊነት ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሊመድብ መሆኑን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እመድታለሁ ካላቸው መካከል ከመቀሌ እና አክሱም በተጨማሪ በአዲግራት፣ በራያ እና በወልድያ ዩኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ የነበሩ መምህራን ተካተዋል።
መምህራኑ ከዛሬ ሰኞ ጥቅምት 22 ጀምሮ እስከ እሮብ ጥቅምት 24፣ 2014 እንዲመዘገቡም ጠይቋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከቀናት በፊት በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በአማራ ክልል በሚገኘው ወልድያ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ሌሎች የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለመመደብ መወሰኑን አሳውቆ ነበር።
በዚህ ሳምንት ከተጀመረ አንድ ዓመት የሚደፍነው በትግራይ ክልል ጀምሮ ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት፣ በትግራይ ክልል ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እና በአማራ ክልል ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወቃል።
በሰኔ ወር መገባደጃ የፌዴራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ትግራይ ክልልን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ጦርነቱ ወደ አጎራባች ክልሎች በመስፋፋቱ በትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሄዱ ተማሪዎች ዘግየት ብሎም ቢሆን በትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ክልሉን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።