አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ጥቅምት 21፣ 2014 ― በኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ ለመስጠት በወጣው ጨረታ የቴሌኮም ዘርፉን የሚቀላቀለው የጨረታ አሸናፊ ኩባንያ በመጪው ጥር ወር ይፋ እንደሚደረግ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ባለፈው መስከረም ወር ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
መንግሥት የቴሌኮሙዩኔኬሽን ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ በወሰነው መሠረት፣ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሁለት ኩባንያዎች ለ15 ዓመታት አገልግሎቱን ማቅረብ የሚችሉበት ፈቃድ ለመስጠት በ2013 ባወጣው ጨረታ ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለው የኩባንያዎች ጥምረት አሸናፊ መሆኑን አይዘነጋም፡፡
ሁለተኛ በመሆን በቻይና የሲልክ ሮድ ፈንድ ድጋፍ ተደርጎለት 600 ሚሊዮን ዶላር ያቀረበው ኤምቲኤን አነስተኛ መጫረቻ በማቅረቡ ሳያሸንፍ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሰበብ አንድ ተጨማሪ ኩባንያ ወደ ገበያው ለማስገባት በመስከረም 2014 ለሁለተኛ ጊዜ በወጣውና እስከ ኅዳር 2014 አጋማሽ ድረስ በሚቆየው ጨረታ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነዱን በማየት የመወዳደሪያ አቅማቸውን ይገልጻሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና በጥር ወር አሸናፊውን ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ ነግረውኛል ብሎ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።
በሁለተኛው ዙር ጨረታ የሚያሸንፈው ኩባንያ ወደፊት የሞባይል በገንዘብ አገልግሎት ለመሳተፍ ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ መጠየቅ እንደሚችል የሚገልጽ መተማመኛ በጨረታ ሰነዱ ላይ መቅረቡን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በመጀመርያው የቴሌኮም ጨረታ ወቅት ለአምስተኛው ትውልድ ፍሪኩዌንሲ (5G) ከ3.5 በላይ ጊጋ ኸርዝ ፍሪኩዌንሲ ለመጠቀም እንደ ገና ፈቃድ መጠየቅ የነበረበትን መሥፈርት፣ በአዲሱ ጨረታ ሰነድ ላይ ከተጠቀሰው በላይ ጊጋ ኸርዝ ለመጠቀም የሚያስቸላቸው ፈቃድ በጨረታው አብሮ መካተቱን አክለው መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በ2013 በወጣው የመጀመርያ ጨረታ የቴሌኮም ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ ዕድል የሰጠ ሲሆን፣ መስከረም 18፣ 2014 የወጣው ሁለተኛው ጨረታ ኩባንዎችን ቀጥታ ወደ ውድድር የሚጋብዝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት በ2013 ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶችን ለመስጠት ባወጣው ጨረታ፣ ለ126 ዓመታት ተይዞ የነበረውን የኢትዮጵያ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ የተቀላቀለው ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ (ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ) በሚል ስያሜ አራት ታዋቂ የግል የቴሌኮም ኩባንያዎችን ይዞ በጥምረት የተቀላቀለ ሲሆን፣ ጥምረቱ ላገኘው የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ያሸነፈበትን 850 ሚሊዮን ዶላር ለመንግሥት ገቢ በማድረጉ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በመጪዎች ሦስትና አራት ወራት ውስጥ አግልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቆ፣ ለደንበኞቹ ዓለም የደረሰበትንና ዘመናዊ የተባለውን የኢንተርኔት አገልገሎት በማቅረብ ተወዳደሪ ለመሆን መዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡