አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 20፣ 2014 ― በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያን ወረዳ 70 ሰዎች መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ሲል በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መታገታቸው ተነግሯል።
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ምንጮቼ ነግረውኛል እንዳለው “የኦነግ ሸኔ ተላላኪዎች” ናቸው ያሏቸው አካላት በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉተን ከተማ ነዋሪዎችን “ዕርዳታ ልትሰጡ ነው” ብለው ሰብስበው ወደ መኪና ካስገቧቸው በኋላ አግተዋቸዋል።
ባሳለፍነው ጥቅምት 15፣ 2014 መነሻቸውን አንገር ጉትን አድርገው ወደ ነቀምት ሲጓዙ የነበሩት ሁለቱ አውቶብሶች፣ በታጣቂዎቹ አማካይነት ውኬ ልጎ መገንጠያ ላይ መታገታቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ኦነግ ሸኔ የታገቱ ተሳፋሪዎች በመኪኖቹ ውስጥ እንዳሉ ወሮ አለልቱ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ተወስደዋል።
ሽብርተኛ በተባለው የሸኔ ታጣቂዎች ታገቱ የተባሉት ነዋሪዎቹ፣ በሁለት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተሳፍረው የነበሩ ሕጻናትና ሴቶች፣ እንዲሁም ሽማግሌዎችን ጨምሮ በቁጥር 70 መሆናቸው ተመላክቷል።
የታገቱት ሰዎች በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉ ማወቅ እንዳልተቻለም ነው የተገለጸው። “የታገቱት ሰዎች መመለስ ያጠራጥረናል” የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ከዚህ በፊት በታጣቂዎቹ ታግተው የነበሩ ሰዎች በሕይወት መመለስ አለመቻላቸውንም አስታውሰዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ዕርዳታ እንዲያደርግ ሲጠየቅ “ከመንግሥት ፈቃድ አልተሰጠንም” የሚል ምላሽ ከመስጠት ውጭ የወሰደው ዕርምጃ የለም።
ከቤታቸው ወጥተው ወደ አጎራባች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች “ስለ ታገቱት ሰዎች ኹኔታ ከከተማው ከንቲባ ምላሽ ስናጣ ወደ ፖሊስ አዛዦች ሔደን ዕርዳታ ብንጠይቅም፣ መፍትሔ ሊሰጡን ፈቃደኞች አልሆኑም” ሲሉ ነው መናገራቸው በዘገባው ተመላክቷል።
ጋዜጣው ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ወደ አንገር ጉትን የፖሊስ አዛዥ ሻምበል ኩምሳ መኮንን የደወልኩ ቢሆንም፣ አዛዡ “ምንም አልተፈጠረም” በማለት ስልካቸውን ዘግተዋል ብሏል።