አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 20፣ 2014 ― የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አሕመድ የአራት ወራት ዕድሜ ያለውን የልብ ታማሚ ጨቅላ የውጭ አገር ሕክምና ወጪ በኩባንያው ሥም እንደሚሸፍኑ አስታውቀዋል።
ባህራን ያሬድ የተባለው የአራት ወራት ከ11 ቀን ዕድሜ ያለው ኮንጀናይታል ኸርት ዲዚዝ የተሰኘ የልብ አፈጣጠር ችግር አጋጥሞት በውጭ አገር ሕክምናውን ለማካሄድ ባለፉት ቀናት በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በስፋት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ሲደረግለት ነበር።
ለጨቅላው የሕክምና ወጪ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰአት ድረስ ከ15 ሺሕ ዶላር በላይ በጎፈንድ ኢ ተሰብስቧል።
ነገር ግን የሚድሮክ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ የገቢ ማሰባሰቢያ ከሚያከናውኑ አካላት ጋር ባደረጉት የመረጃ ልውውጥ ባህራን ያሬድ ወደ ሕንድ ሀገር ሄዶ ህክምናውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ሙሉ ወጪ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስም እንደሚሸፈኑ አረጋግጠዋል።
ሕፃን ባህራን ያሬድ ባለፉት ወራት በጥቁር አንበሳ የልብ ህክምና ማዕከል እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህክምና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ቤተሰቦቹ የገለጹ ሲሆን፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በሀገር ውስጥ እየተሰጠው ያለው ህክምና እንዳልተሳካ ገልጾ ለከፍተኛ ህክምና ወደ ውጪ ሀገር ሄዶ መታከም እንደሚገባው ማሳወቁም ነው የተነገረው።