አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 20፣ 2014 ― የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የስራ ጊዜ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በዛሬው እለት ያካሄዳል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ በሚካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልና ህዝበ ውሳኔ ውጤትን ያፀድቃል ተብሎ ተጠብቋል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው እለት የሚያጸድቀው ውሳኔ፣ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ የተካሄደውን የሕዝብ ውሳኔ ውጤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ ማሳወቁን ተከትሎ የሚደረግ ነው፡፡ በዚህም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 11ኛ ክልል መሆኑን እውቅና ይሰጣል ነው የተባለው፡፡
ከምክር ቤቱ ውሳኔ በኋላ የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሚያደርገው ስብሰባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ ያደርጋል መባሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ 11ኛ ክልል የሚሆነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደው ባለፈው መስከረም ወር መገባደጃ ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በደቡብ ክልል አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ማለትም ምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮ፣ ካፋ፣ ዳውሮ፣ ሸካ ዞኖችና ኮንታ ልዩ ወረዳ ‹‹ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመሥረታቸውን እደግፋለሁ›› የሚለው አማራጭ 1 ሚሊዮን 221 ሺ 92 ድምጾች አግኝቷል፡፡ በአንጻሩ ‹‹የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸውን እደግፋለሁ›› የሚለው ምርጫ 24 ሺሕ 24 ድምጽ ማግኘቱን ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡