Sunday, September 22, 2024
spot_img

በደሴ ከተማ በተፈጸመ የመድፍ ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት መቀጠፉን የከተማው ከንቲባ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 19 2014 ― በደቡብ ወሎ ዞን መቀመጫ በደሴ ከተማ ላይ በተተኮሱ የመድፍ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የከተማዋ ከንቲባ ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እንደ ከንቲባው አቶ አበበ ገብረመስቀል ከሆነ ወደ ከተማው የመድፍ አረር የተተኮሰው ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 18፣ 2014 ከሰዓት በኋላ ነው፡፡ ከንቲባው ጥቃቱን የሰነዘሩት የሕወሓት ኃይሎች ናቸው ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተባብሶ የቀጠለው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ውጊያ ከሰሞኑ በደሴ ከተማ አቅራቢያ እየተካሄደ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከንቲባው እንደገለጹት ትላንት በሕወሓት ተሰንዝረዋል ያሏቸው መድፎች ወደ ደሴ ከተማ የተተኮሱት ከሰዓት በኋላ በግምት 9 ከ30 ላይ ሲሆን፣ ሦስት የተለያዩ ቦታዎች የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሕወሐት ኃይሎች በአጠቃላይ አምስት የመድፍ አረሮችን በከተማዋ ላይ ተኩሰዋል የተባለ ሲሆን፤ ሁለቱ መናፈሻ በሚባለው የከተማዋ አካባቢ፣ ሁለቱ ዳውዶ በሚባለው ስፍራ እንዲሁም ቀሪው አንድ ደግሞ እርሻ ሰብል ከሚባለው ቦታ ላይ መውደቁን ነው ከንቲባው የተናገሩት፡፡

በተለይ እርሻ ሰብል እና መናፈሻ በተባሉት የከተማዋ ስፍራዎች ላይ ያረፉት አረሮች ሰላማዊ ነዋሪዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ እንደሆነና ዳውዶ በተባለው አካባቢ ላይ የተተኮሰው መድፍ በሰው ላይ ጉዳት ሳያደርስ ሜዳ ላይ መውደቁን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

የመድፍ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በጦርነቱ ምክንያት ከሰሜን ወሎ ዞን የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉበትና እርዳታ የሚያገኙበት ስፍራ እንደሚገኝበት ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

ከደሴ ከተማ ውጪ ከሚገኝ ስፍራ በህወሓት ኃይሎች በከተማዋ ላይ ተፈጸመ በተባለው በዚህ የከባድ መሳሪያ ጥቃት የተገደለውና የቆሰሉት ንፁሃን ሰዎች መሆናቸውን አቶ አበበ ገብረ መስቀል ተናግረዋል።

በሰዎች ላይ ሞትና የመቁሰል ጉዳት የደረሰው እርሻ ሰብል እና መናፈሻ በተባሉት ሁለት ስፍራዎች ላይ ሲሆን፣ ‹‹በአንደኛው ቦታ ሦስት ንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ከእነዚህም መካከል አንዱ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉን›› ከንቲባው ገልጸዋል። በሌላኛው ስፍራ ላይ በተተኮሰው የመድፍ አረር ደግሞ አንድ ሰው መቁሰሉን ጨምረው አቶ አበበ አስረድተዋል።

በዚህ የመድፍ ጥቃት የሞተው ግለሰብ እና የቆሰሉት ሰዎች የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ወይም ተፈናቅለው ከሚገኙት ሰዎች መካከል እንደሆኑ ለመለየት የከተማዋ ባለሥልጣናት እያጣሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የመድፍ ጥቃት ያስተናገደችው የደሴ ከተማ በትግራይ ተጀምሮ ወደ ሰሜን ወሎ አካባቢዎች በተስፋፋው ጦርነት ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተጠለሉባት ናት፡፡

በከተማዋ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ እንደሚሰማም ቢቢሲ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡  

መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው የሕወሓት ሊቀመንበር ሆኑት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ረቡዕ ጥቅምት 17፣ 2014 ቡድናቸው በሰሜን ወሎ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ በተናገሩበት ጊዜ ተዋጊዎቻቸው ‹‹በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ቂም በቀል የለም›› በማለት የደሴና ኮምቦልቻ ነዋሪዎች እንዲረጋጉ ጠይቀው ነበር። ሆኖም ቡድኑ አሁን ወደ ደሴ ሰንዝሮታል ስለተባለው የመድፍ ጥቃት ያለው ነገር የለም፡፡

ከንቲባው አቶ አበበ በበኩላቸው የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ ደሴም ሆነ ኮምቦልቻ ሊገቡ እንደማይችሉ ጠቅሰው፣ አሁን ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ መሆኗን መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከሰሞኑ ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን እየሰነዘረ ይገኛል፡፡ አየር ኃይሉ በትላንትናው እለት የሰነዘረው ጥቃት ኢላማ ያደረገው መቐለ የሚገኘው መሥፍን ኢንጅነሪንግን መሆኑን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን በደረሰው የአየር ድብደባ የሰዎች ህይወት ማለፉንና መጎዳታቸውን የአይደር ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና ክፍል ኃላፊ ግርማይ ለገሰ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ በጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ ተብሎ የሚነገረው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በተለያየ የሀሰተኛ መረጃ ለማምታት የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው ብለውታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img