Saturday, November 23, 2024
spot_img

በአማራ ክልል የሁለተኛውን ዙር የአስተራዜኔካ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ቁጥር ከ29 በመቶ እንደማይበልጥ የክልሉ ጤና ቢሮ አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 17 2014 በአማራ ክልል የመጀመሪያውን የአስተራዜኔካ የኮሮና መከላከያ ክትባት ከወሰዱ 420 ሺሕ በላይ ሰዎች መካከል ሁለተኛውን ዙር ክትባት የወሰዱ ከ29 በመቶ እንደማይበልጡ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው የክትባት ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞን ጠቅሶ ዶይቼ ቬለ እንደዘገበው ካለፈው ዓመት መጋቢት ጀምሮ በክልሉ ሁሉም የጤና ተቋማት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህም ለክልሉ ከደረሰው የአስትራዜኔካ ክትባት ውስጥ 96 ከመቶው በመጀመሪያ ዙር ለ420 ሺህ 372 መሰጠቱን ገልጸዋል።

የአስተራ ዜኔካ ክትባት በሁለት ዙር የሚሰጥ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ወርቅነህ፣ የመጀመሪያውን ክትባት ከወሰዱ ሰዎች መካከል 122 ሺህ 765ቱ ወይም 29 ከመቶ ብቻ ሁለተኛውን ዙር መውሰዳቸውን አመልክተዋል። በሌላ በኩል ክልሉ 240 ሺህ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባለ ክትባት ማግኘቱን የተናገሩት አስተባባሪው እስካሁን 54 ሺህ ያህል ሰዎች ክትባቱን መውሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡

 ከወቅታዊው የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞም በርካታ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ወርቅነህ፣ 33 ሺህ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች የኮቪድ ክትባት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ክትባት ውጤታማ እንደነበር የተናገሩት አስተባባሪው፣ በምሥራቅ አማራ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስና ህብረተሰቡ ስለ ክትባቱ ያለው ዝቅተኛ ግንዛቤና አሉባልታዎች ለሁለተኛው ዙር ክትባት መቀዛቀዝ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡

በበሽታው የሚሞተው ሰው ቁጥር እየጨመረ መሆኑንና በዋናነት ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ያልተከተቡት በመሆናቸው ሕብረተሰቡ ይህንኑ ተረድቶ ክትባቱን ያለምንም ጥርጣሬ እንዲወስድና ሕይወቱን እንዲታደግ ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ እንዳስታወቀው በአማራ ክልል እስከ ትናንት ጥቅምት 16፣ 2014 ድረስ 399 ሰዎች ከኮሮና ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img