Monday, October 14, 2024
spot_img

ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የታሸጉ ድርጀቶች አስተዳዳሪ ተሾሞላቸው ሥራ ሊጀምሩ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 17 2014 ― በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሽብርተኝነት የተሰየመውን ሕወሓት ይደግፋሉ ተብለው የታሸጉ ፋብሪካዎችና ሌሎች የንግድ ድርጅቶች አስተዳዳሪ ተሾሞላቸው በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ ተሰምቷል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት በርካታ የንግድ ድርጅቶችና ሆቴሎች  የንግድ ሕጉን በመጣስና የሕወሓትን የሽብር ተግባር በመደገፍ ተጠርጥረው በአዲስ አበባ ፖሊስ ታሽገው እንዲቆዩ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ የንግድ ድርጅቶች ተመልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ ቢደረግም፣ ቁጥራቸውን በግልጽ ለማወቅ ያልተቻሉ ትልልቅ ሆቴሎች ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ ከሆቴሎቹ መካካል ካሌብ፣ ኔክሰስ፣ አክሱም፣ ንግሥተ ሳባ፣ ሐርመኒ ሆቴል እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ በዛሬው እትሙ በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉትን የንግድ ድርጅቶችና ሆቴሎች አስተዳዳሪ ተሾሞላቸው ሥራቸውን እንደገና እንዲቀጥሉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ ነግረውኛል ብሏል፡፡ ነገር ግን በድርጅቶቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ የሚቀጥል መሆኑን አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀል የተጠረጠሩትን ተቋማትና ግለሰቦች ወደ ፍርድ እንደሚያቀርብ በመጥቀስ፣ የከተማ አስተዳደሩ ደግሞ ድርጅቶቹን ለመክፈት ወይም ላለመክፈት አስተዳደራዊና የወንጀል ሕጉን መሠረት በማድረግ ውሳኔ እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

በሆቴሎችም ሆነ በንግድ ድርጅቶች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ሥራ አጥ መሆን እንደሌለባቸው የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ ድርጅቶቹ በታቻለ መጠን ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ለሕወሓት ድጋፍ ያደርጋሉ የተባሉ ወይም በድርጅቶቹ የበላይ ኃላፊዎች አማካይነት ይዘወራሉ ተብለው የተጠረጠሩ ሕንፃዎች፣ በፍርድ ቤት ውሳኔ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አስተዳዳሪ ሆኖ እያከራያቸው፣ የባንክ ብድር ካለባቸውም እየከፈሉ ሥራ ላይ እንዲቆዩ መደረጉን አውስተዋል፡፡

በምርመራ ላይ ያሉትን ሆቴሎችንም ሆነ ፋብሪካዎችን ቀጣይ ዕድል ለማወቅ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ውሳኔ ያሰጥባቸዋል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የታሸጉና የተዘጉ ሆቴሎች በዋነኝነት ገንዘብ በማሸሽ፣ ጦርነቱን ከሕወሓት ጎን በመሆን በፋይናንስ በማገዝ በሕገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ማስረጃ የተገኘባቸው መሆኑንና ጉዳያቸውም ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ሚኒስተር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img