Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአሜሪካ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ከትጥቅ እንቅስቃሴ ውጭ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን ያሳተፈ ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ የውሳኔ ሐሳብ አጸደቀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 16 2014 ― የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ጉዳይ ኤች አር 445 የተሰኘውን የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ አጽድቋል፡፡

ይህ ተሻሽሎ መቅረቡ የተነገረው የውሳኔ ሐሳብ በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት መፍትሔ እንዲያገኝ መንግሥት ከሕግ ውጭ የታሰሩ የተቃዋሚ መሪዎችን እና ደጋፊዎችን፣ ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችን እንዲፈታ እና ከትጥቅ እንቅስቃሴ ውጭ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን ያሳተፈ ብሔራዊ ውይይት እንዲያደርግ ይጠይቃል።

 

በተጨማሪም የውሳኔ ሐሳቡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ ግጭቶችን እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያወገዘ ሲሆን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የሚሳተፉ ሁሉም አካላት ግጭቶችን እንዲያቆሙ፣ ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ተደራሽነትን እንዲፈቅዱ እና የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ ከገለልተኛ መርመሪዎች ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።

በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የተናገሩት በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ፣ የዓለም ጤና እና የሰብዓዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ካረን ባስ ውሳኔውን የመሩት ‹‹በብሔረሰብ፣ በፖለቲካ እና በታሪክ ለተወሳሰበ ለዚህ ሁለገብ ግጭት ሠላማዊ የድርድር መፍትሄ ማየት ስለምፈልግ ነው›› ብለዋል።

ሕወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ በጀመረው ጥቃት ሠራዊቱ ምላሽ መስጠቱትን ያስታወሱት ባስ፣ ‹‹ለውጥ ሳይደረግ እና በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይኖር ግጭቱ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ይዘልቃል የሚል ስጋት አለኝ›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ኬረን ባስ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን ማነጋገራቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ከግጭቱ ጋር አያይዘው ኢትዮጵያ ከባይደን አስተዳደር የሚመጣ ማዕቀብ ስጋት ላይ መሆኗን እንዲሁም ሁከቱ ከቀጠለ በአጎዋ ተሳታፊነት ልትወጣ እንደምትችል አሳስቦኛል ያሉት ባስ፣  ‹‹ይህ ግጭት እና የሰብዓዊ ቀውሱ ውጤት ኢትዮጵያ የአህጉሩ ምሰሶ ሆና የመቀጠል አቅሟን እየሸረሸረ በመሆኑ መቀየር አለብን›› ብለዋል።

ምክር ቤቷ በኢትዮጵያ ጉዳይ የውሳኔ ሐሳብ ያጸደቀው አሜሪካ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት እንዲቆም ተደርጎ ተፋላሚዎች ወደ ጠረጴዛ ካልመጡ ወደ እርምጃ እንደምትሄድ በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች፡፡

ከሦስት ሳምንት በፊት አዲሱን ካቢኔያቸውን ያዋቀሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በአገሪቱ ብሔራዊ ውይይት እንደሚደረግ በወቅቱ ያሳወቁ ሲሆን፣ ይህ ውይይት የሚያሳትፈው በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ኃይሎች ብቻ እንደሚሆን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ከትላንት በስትያ ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር ጦርነቱ ቆሞ የታጠቁ አካላትን ጭምር ያሳተፈ ብሐየራዊ ውይይት ሊደረግ ይገባል ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img