Wednesday, October 9, 2024
spot_img

የአውሮፓ ኅብረት እና ጣሊያን በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎች አዘዋዋሪው ኪዳኔ ዘካሪያስን ከኔዘርላንድ መንግሥት ጋር አፈልልጎ ለመያዝ መስማማታቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 16 2014 የአውሮፓ ኅብረትና የጣልያን መንግሥት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሰማራው ኪዳኔ ዘካሪያስን አፈላልጎ በድጋሚ ለማሳሰር ከኔዘርላንድ መንግስት ጋር በጥምረት ለመስራት መስማማታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን የዘገበው ሚድል ኢስት ዐይ ነው፡፡

ኪዳኔ ዘካሪያስ በሊቢያ በረሃ ከ2008 ጀምሮ በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የሶማሊያ ዜግነት ያላቸው ስደተኞችን አግቶ በማሰቃየትና በመግደል ሥሙ የሚነሳ ሲሆን፣ በየካቲት 2012 በአዲስ አበባ ተይዞ ከዓመት እስራት በኋላ ከእስር አምልጦ አሁን መዳረሻው አይታወቅም።

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ከቀናት በፊት ኤርትራዊው ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ተይዞ በወንጀል እንዲጠየቅ በሚል በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ እንዳካተተው መነገሩ አይዘነጋም፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የአውሮፓ ኅብረት ፖሊስ ከኔዘርላንድ ጋር ለመሥራት ሲስማማ፣ የብዙ አፍሪካዊያን ስደተኞች ማረፊያ የሆነችው ጣሊያንም ቡድኑን ተቀላቅላለች፡፡

በአገራቱ ፖሊስ አሰሳ የሚደረግበት ኪዳኔ የሚመራው የወንጀል ቡድን በሊቢያ ባኒ ወሊድ የተሰኘ ከተማ ላይ በአንድ ጊዜ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የሚይዝ ማጎረያ ቤት ውስጥ ለታፈኑት ስደተኞች ከነ ሕይወታቸው እንዲለቀቁ ከቤተሰቦቻቸው እስከ 200 ሺህ ብር እንዲከፍሉ ይጠየቅ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል፡፡ ክፍያው እንዲፈጸም ስደተኞችን በመደብደብ በማስራብ ጥፍሮቻቸው በመንቀል የቀለጠ ፕላስቲክ በባዶ ገላቸው በማፍሰስ የሚያሰቃይ ሲሆን፣ ሴቶች እና ሕጻናት ደግሞ እንዲደፈሩ ያደርጋል። በዚህ መሀል የታጋቾች ቤተሰቦች ገንዘቡን ከከፈሉ የሚለቀቅላቸው ሲሆን፣ አቅም የሌላቸው ስደተኞች ደግሞ እዚያው ተገድለው አስከሬናው ወደ በረሃው ይወረወራል።  

ኤርትራዊው ኪዳኔ ዘካርያስ ከኢትዮጵያ እስር ቤት ካመለጠ በኋላ በኢትዮጵያ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ሁለት ኢትዮጵያውያን አሰቃይቶ በመግደል ወንጀሎች የእድሜ ልክ ፍርድ ተላልፎበታል፡፡

በስደተኞች ጉዳይ ክትትል የምታደርገው ኤርትራዊት አክቲቪስቷ ሜሮን እስጢፋኖስ እንደምትለው ከሆነ ኪዳኔ ዘካሪያስ ከኢትዮጵያ እስር ቤት ለማምለጥ በሰዎች ስቅይት ካከማቸው በርካታ ሚሊዮን ዶላር ሥሙ ላለተጠቀሰ አንድ ባለስልጣን የ10 ሚሊዮን ብር በጉቦ መልክ በመስጠት ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ በማቅናት በአሁኑ ሰዓት ወደ ሊቢያ ሳይመለስ አይቀርም፡፡  

በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የእድሜ ልክ ፍርድ ሲተላልፍበት፣ በኪዳኔ ስም ገንዘብ በመቀበል አብራው የተከሰሰችው ሳባ መንድር ኃይሌ የተባለች ሴት የ12 ዓመት እስር ተፈርዶባታል። ሌላው የእሱ ተባባሪ እንደሆነ የሚነገረው እና ዋሊድ በሚል ስም የሚታወቀው ተወልደ ጎይቶም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበታል፡፡

እንደ ዘገባዎች ከሆነ በፈረንጆቹ ከ2014 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ኪዳኔ ዘካሪያስ እና አባሪው ተወልደ ጎይቶም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሊቢያ ውስጥ አዘዋውረዋል። የዓለማችን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ኪዳኔ ከካርያስን ‹‹የዓለማችን እጅግ አደገኛ እና ጨካኝ ሰው አዘዋዋሪ›› በሚል ይገልጹታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img