Sunday, November 24, 2024
spot_img

ጠ/ሚ ዐቢይ መንግሥታቸው የትግራዩን ግጭት በምን ያህል ጊዜ ለመቋጨት እየሠራ እንደሚገኝ በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 16 2014 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት መንግሥት የትግራዩን ግጭት በምን ያህል ጊዜ ለመቋጨት እየሠራ እንደሚገኝ በፓርላማ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ የጠየቁት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው በሕዝብ የተመረጡት የፓርላማ አባላት ናቸው፡፡

ፓርቲው እንዳስታወቀው አራቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄያቸውን ባለፈው ሳምንት ዐርብ ጥቅምት 12፣ 2014 በተወካያቸው አማካይነት ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ በደብዳቤ አቅርበዋል።

አባላቱ ባስገቡት ደብዳቤ የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በይዞታው ሥር ከነበሩ ቦታዎች ለቆ እንዲወጣ መንግሥት ሲወስን በትግራይ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ከግጭት ረፍት እንዲያገኙ በማሰብ እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፣ ነገር ግን ግጭቱ ከመቀነስ ይልቅ እንዲያውም አዳዲስ አካባቢዎችን ወደ ግጭት ቀጠናነት እየጨመረ መምጣቱን እንዲሁም በቅርቡም የደቡብ ወሎ አካባቢዎችን ስጋት ውስጥ እንደከተተ መገለጹን ፓርቲያቸው አስታውቋል፡፡

ይህን መሠረት በማድረግ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው መንግሥታቸው በምን ያህል ጊዜ ግጭቱን ቋጭቶ ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ፣ ዕቅዱን ለማሳካት ከማኅበረሰቡ እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቀው ምን እንደሆነ፣ ከመረጃ ፍሰት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ክፍተት ለማረም እየተሠራ ያለ ሥራ ካለ እንዲሁም አሁን አገሪቱ የገባችበት ዓይነት ችግር ውስጥ ተመልሳ እንደማትገባ የሚያረጋግጥ ሥራ እየተሠራ ከሆነ ለምክር ቤቱ አባላት እንዲያብራሩ ነው የተጠየቁት።

በ2008 የወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወር አንድ ጊዜ የቃል መልስ የሚሰጥበት የአንድ ሰዓት የጥያቄ ጊዜ ይኖረዋል›› ሲል ይደነግጋል። በደንቡ መሠረት ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ የምክር ቤት አባል ጥያቄውን ከአስር ቀን በፊት ለምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት። ሆኖም ‹‹ለህዝብ ጠቀሜታ ያለው አስቸኳይ ጥያቄ›› በሚቀርብበት ጊዜ ከአስር ቀን ባነሰ ማስታወቂያ በአፈ ጉባኤው ፍቃድ ለምክር ቤቱ ሊቀርብ እንደሚችል ደንቡ ያስቀምጣል።

ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የኢዜማ ተወካዮች፣ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ ነው የተባለው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img