አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 16፣ 2014 ― ግዙፉ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ፌስቡክ በአማራ ክልል እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት ‹‹ፋኖ›› ከተሰኘው ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉና ሁከት አባባሽ ጥሪዎች ሲያዛምቱ በነበሩ አካውንቶች ላይ መረጃ እያለው እርምጃ አልወሰደም በሚል ወቀሳ ተሰንዝሮበታል፡፡
ሁከት ቀስቃሽ ናቸው የተባሉት ከፋኖ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት የፌስቡክ አካውንቶች አንዳንዶቹ መቀመጫቸውን ጎረቤት አገር ሱዳን ባደረጉ ሰዎች የሚተዳደር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ አካውንቶች የትጥቅ ትግልን የሚያበረታቱ መልእክቶችን ከማሰራጨት ባሻገር፣ ምልመላ እና የገንዘብ መዋጮ ይሰበሰብባቸው እንደነበር ሲኤኤን ተመልክቼዋለሁ ያለውን ለአሜሪካ ሕግ መምሪያ ምክር ቤት ከቀርቡት ምስጢራዊ የኩባንያው ሰነዶች መካከል ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው ኢትዮጵያን ‹‹ለግጭት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት›› በሚለው ምድብ ቢያስቀምጣትም፣ የኩባንያው ሠራተኞች ፌስቡክ በኢትዮጵያ ለግጭት አባባሽነት እየዋለ ስለመሆኑ ላቀረቧቸው ጥቆማዎች ግን ኩባንያው ምላሽ እንዳልሰጠ ከሰነዶች መረዳት መቻሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሰነዶቹ የውጭ መንግሥታትና ድርጅቶች በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርና ግጭትን ለመስበክና ለማሰራጨት ፌስቡክን እንደተጠቀሙበት ያሳያሉ ነው የተባለው፡፡
ፌስቡክ ኩባንያ ከዚሁ ጋር በተገናኘ በቅርቡ ከቀድሞ ሠራተኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ ሀገራት የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መግታት እየቻለ አላስቆመም የሚል ውንጀላ እንደቀረበበት አይዘነጋም፡፡ ይህንኑ ለሁለት ዓመታት ያህል በኩባንያው የሠሩት የዳታ ሳይንቲስቷ ፍራንሴስ ሃውገን በአሜሪካ ሕግ አውጭ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ተናግረዋል።
እንደ ቀድሞዋ የኩባንያው ባልደረባ ከሆነ ፌስቡክ በተለይ ከእንግሊዝኛ ውጭ ባሉ ቋንቋዎች የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በአግባቡ አይቆጣጠርም፡፡ ኩባንያው የጥላቻ ንግግርን ከመቆጣጠር ይልቅ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ለሚስገባው ትርፍ እንደሆነም ሠራተኛዋ አክለው ገልጸው ነበር፡፡
ፌስቡክ የሚያሰራጫቸውን መልእክቶቹ በሥርዐት አልተቆጣጠረውም የተባለው ‹‹ፋኖ›› የተሰኘው ኢ መደበኛ ታጣቂ ቡድን፣ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ አንድ ዓመት ሊደፍን በቀረበው ጦርነት በትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ፣ ማፈናቀል እና ሌሎች ዘግናኝ የመብት ጥሰቶችን ፈጽሟል በሚል አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በሌሎችም ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ውንጀላ የሚቀርብበት ነው፡፡