Tuesday, October 8, 2024
spot_img

ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ በአምስት የመንግሥት ተቋማት ላይ ክስ ተመሠረተ

 

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 ― በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ከፊት ያሰለፈው አመራር ከመምጣቱ አንድ ዓመት በፊት ተፈጽሟል ከተባለ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የቀድሞ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (ፍትሕ ሚኒስቴር)፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ላይ የፍትሐ ብሔር ክስ ተመሥርቷል፡፡

ክሱ የተመሠረተባቸው መንግሥታዊ ተቋማት፣ ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) ላይ የሕጓ አካል ያደረገቻቸውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ስቃይ ስምምነት አንቀጽ 1 እና 2(1)፣ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች (ICCPR) አንቀጽ (7) እና የአፍሪካ ሕዝቦችና ሰዎች መብት ሰነድ አንቀጽ  (5) እና (6)ን ድንጋጌዎች በመተላለፍ መሆኑን ክሱ እንደሚያብራራ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብኛል ያሉትና በተቋማቱ ላይ ክስ የመሠረቱት አቶ ዮናስ ጋሻው ደመቀ የተባሉ ተበዳይ ሲሆኑ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባኛል ያሉት፣ ‹‹በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረሃል›› ተብለው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ጥር 5፣ 2009 እስከ ሰኔ 15፣ 2010 ድረስ መሆኑም በክሱ ተጠቁሟል፡፡

የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት ዓለም አቀፍ የስምምነት ድንጋጌዎች ተጥሰው ሰቅሎ (አንጠልጥሎ) በጎማ ዱላና ኤሌክትሪክ ገመድ ግርፋት፣ በሰውነት ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መልቀቅ እንደተፈጸመባቸውም በክሱ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ከሳሽ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ መራመድ እንደማይችሉ፣ ለአዕምሮ ችግርና ለከፍተኛ የሥነ ልቦናዊ ቀውስ መዳረጋቸውንና መቶ በመቶ ቋሚ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በሙያቸው ሠርተው ያገኙት የነበረው ገቢ የባለቤታቸውን ጨምሮ መቋረጡንና ሌሎች አካላዊና የሥነ ልቦና ችግር እንደደረሰባቸውም ክሱ ያብራራል፡፡

የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት ከሳሽ የተጠቀሱት ቋሚ ጉዳቶች የደረሱባቸው፣ በወንጀል ጉዳይ እንደሚፈለጉ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ፌዴራል ፖሊስ በወቅቱ በሥራ ላይ የነበረውን የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ድንጋጌን በመተላፍ፣ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከአንድ ወር በላይ ታስረው እንዲቆዩ በማድረጉና ያልፈጸሙትን ወንጀል ‹‹ፈጽሜያለሁ›› ብለው እንደሚያምኑ፣ በተለያዩ የፖሊስ አባላት ተሰቅለው በመገረፋቸው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲለቀቅባቸው በመደረጉና ከሰኔ 15፣ 2009 ጀምሮ ክስ ተመሥርቶባቸው ቅሊንጦ የቀጠሮ እስረኞች ማቆያ ከተወሰዱ በኋላም የደረሰባቸውን አካላዊ ጉዳት እንዳይታከሙ በመከልከላቸው መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ በጊዜ ቀጠሮ ለአራት ወራት ፍርድ ቤት ከተመላለሱ በኋላ ለጥርጣሬ የሚያበቃ ማስረጃ በመታጣቱ በነፃ ወይም በዋስ መለቀቅ ሲኖርባቸው፣ ፍርድ ቤቱ ምንም ሳይል መዝገቡን ዘግቶ ለስድስት ወራት ያህል በማዕከላዊ ሲገረፉና ሲደበደቡ ቆይተው፣ ክስ ከተመሠረተባቸው በኋላም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታቸውን እያሰማ ምንም ዓይነት ትዕዛዝ ባለመስጠቱ ጉዳቱ እየባሰ መምጣቱን ክሱ ይጠቁማል፡፡

በአጠቃላይ ከሳሽ የተያዙበት ሁኔታ ሕገወጥ መሆኑን ቢያመለክቱም እንዳልተመረመረላቸው፣ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታቸው አለመከበሩን፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት (ፍትሐዊ ዳኝነት) አለማግኘታቸውን ክሱ አብራርቶ፣ ከሕግ ውጭ መያዛቸው፣ በሕግ ከተፈቀደው ውጭ በምርመራ ክፍል ታስረው መቆየታቸው፣ የስቃይ ድርጊት ተፈጽሞባቸው ሳለ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ሕክምና እንዳያገኙ መከልከሉና በፍርድ ቤቶቹም ፍትሐዊ ዳኝነት ባለማግኘታቸው፣ የሚቆጣጠራቸው መንግሥት (የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት) እና ተቋማቱ ተጠያቂ እንዲሆኑ ክሱ መቅረቡን የክስ ሰነዱ ያብራራል፡፡

ተከሳሹ ባቀረቡት ክስ መሠረት ተከሳሽ ተቋማት በአጠቃላይ ለደረሰባቸው አዕምሯዊና አካላዊ ጉዳት 9 ሚሊዮን 821 ሺሕ 339 ብር የካሳ ክፍያ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከሳሽ ለደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉም ተቋማት ባልተነጣጠለ ሁኔታ ሙሉ ኃላፊነት አለባቸው ተብሎ እንዲወሰንላቸው፣ የተፈጸመባቸው ድብደባና ስቃይ፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕገ መንግሥቱ አካል ያደረገቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች የጣሰ ነው እንዲባልላቸው፣ ተቋማቱ ሥልጣን ባለው አካል ትዕዛዝ በመስጠት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጽሙ በታዘዙ የፌዴራል ፖሊስና ማረሚያ ቤት ሠራተኞችና ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ክስ እንዲያቀርቡ እንዲታዘዝላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማናቸውም ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች አያያዝና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የስቃይ ተግባር እንዳይፈጸምና ሥውር እስር እንዲቀር ትዕዛዝ እንዲሰጥና ሌሎችም ትዛዝ እንዲሰጥላቸው በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት የፍትሐ ብሔር ክስ ዳኝነት ጠይቀዋል ተብሏል፡፡

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img