አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 13፣ 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶንዮ ብሊንክን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ መምክራቸው ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ እንዳስታወቁት፣ ሁለቱ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ሰብአዊ ቀውስ አስመልክቶ ተነጋግረዋል፡፡ አክለውም ባለስልጣናቱ በትግራይ ያለው ግጭት ተፋላሚ አካላት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም በትብብር መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውንም ኔድ ፕራይስ አክለዋል፡፡
በትግራይ የሰብአዊ አቅርቦት ለማድረስ እየሠራ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በትላንትናው እለት ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ የሰብዓዊ የአየር አገልግሎቶች አውሮፕላኑን ቢልክም፣ በመቐለ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ተቆጣጣሪዎች እንዳያርፍ በመከልከሉ ወደ አዲስ አበባ መመለሱን በድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በኩል ገልጧል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ወደ ትግራይ የሚላከው የሰብአዊ አቅርቦት በአግባቡ እንዳይተላለፍ በመንግስት በኩል እክል ተፈጥሯል ሲል ቅሬታዎችን ሲያቀርብ የቆየ ቢሆንም፣ መንግስት በበኩሉ ችግር ፈጣሪው ሕወሓት ነው ይላል፡፡
በሌላ በኩል በትግራይ እንዲሁም በአዋሳኝ አፋር እና አማራ ከፍተኛ ሰብአዊ ምስቅልቅል ያስከተለው ጦርነት እንዲቆም የምትወተውተው አሜሪካ፣ የጦርነቱ ተፋላሚ አካላት ወደ ጠረጴዛ የማይመጡ ከሆነ በኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል በፕሬዝዳንትዋ ጆ ባይደን በኩል ትእዛዝ መፈረሟ አይዘነጋም፡፡