አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 13፣ 2014 ― በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት የጉጂ እና ቦረና ዞኖች 395 ሺሕ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯል፡፡
በዞኖቹ ለምግብ እጥረቱ ሰበብ የሆነው የዝናብ እጥረት መሆኑን የሁለትም ዞኖች የአደጋ ስጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊዎች ነግረውኛል ብሎ ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
የጉጂ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ገመቹ እንደገለጹት፣ በዞኑ በሚገኙ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ገበሬዎች ባለፈው የምርት ጊዜ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት በቂ ምርት አላገኙም ያሉ ሲሆን፣ በጉጂ በአሁኑ ወቅት በዞኑ ከሚገኙት 13 ወረዳዎች መካከል በስድስቱ ድርቅ ተከስቷል፡፡
ይህን ተከትሎም በዞኑ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 229 ሺሕ ያህል ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ከእነዚህ የምግብ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች መካከል ሴቶች እና ሕፃናት እንደሚገኙበት ነው የተገለጸው፡፡
በሌላ በኩል የቦረና ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኃላፊ አቶ ሊበን ከበደ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙት ሁሉም ዞኖች በሚባል መልኩ በድርቅ ተመተዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ከሆነ በአሁኑ ወቅት 166 ሺሕ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡
በዞኖቹ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ የመንግስት እና የግል ተቋማት ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው፣ ከችግሩ ስፋት አንጻር ድጋፉ አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡