አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 13፣ 2014 ― በትላንትናው እለት ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ ያቀናው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የተመድ) ሰብዓዊ የአየር አገልግሎቶች አውሮፕላን በመቐለ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ተቆጣጣሪዎች እንዳያርፍ በመከልከሉ ወደ አዲስ አበባ መመለሱን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ገልጸዋል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደ ትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ ከትላንት አመሻሽ ጀምሮ ማገዱን አስታውቋል፡፡
ቃል አቀባዩ እንዳሉት 11 ሰዎችን የጫነው አውሮፕላን ወደ መቐለ ለሚያደርገው ጉዞ ከአዲስ አበባ ሲነሳ ከፌዴራል መንግሥት ባለስልጣናት ፍቃድ ያገኘ ቢሆንም፣ በመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ተቆጣጣሪዎች በከተማው እንዳያርፍ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል።
አውሮፕላኑ አዲስ አበባ ተመልሶ በሰላም ማረፉን የተናገሩት ዱጃሪክ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ጉዳዩን በጥንቃቄ እያጠኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የሰብአዊ እርዳታ የጫነው አውሮፕላን በትላናትናው እለት ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ መንግስት ካካሄደው የአየር ጥቃት ጋር ተያያዥነት እንዳለው ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩን በተመለከተ የተናገሩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ‹‹በራሳቸው ምክንያት ካልሆነ በስተቀር የአየር ድብደባው እና የሰብአዊ እርዳታ ጫኝ አውሮፕላን እንቅስቃሴ አይገናኝም›› ብለዋል፡፡ ሰዓቱ የተለያየ መሆኑን የገለጹት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ፤ ‹‹መዳረሻዎችም የተለያዩ ናቸው›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ክልከላው የተደረገው በመቐለ መሆኑን አረጋግጠው ድርጅቱ በረራዎቹን ሙሉ ለሙሉ ሰርዟል ብለዋል፡፡ ይኸው የበረራ እገዳ ለምን ያህል ጊዜ የሚቆይ እንደሆነ ግን የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ የአገር መከላከያ ሠራዊት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ትግራይን መልቀቁን ተከትሎ መቐለን ጨምሮ የተቆጣጠረው የሕወሃት ቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ የተመድ አውሮፕላን ትላንት በተሰነዘረው የአየር ጥቃት ሰበብ በከተማው የማረፍ እቅዱ ማስተጓጎሉን አስፍረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በተያዘው ሳምንት ለአራት ጊዜ ያህል ወደ መቐለ ከተማ የአየር ጥቃት መሰንዘሩን መንግስት አስታውቋል፡፡ በትላንትናው እለት የተሰነዘረው ጥቃት ‹‹የህወሓት ማሰልጠኛ ማዕከል›› ኢላማ መደረጉን መንግስት ቢያስታውቅም፣ የሕወሓት ሰዎች ጥቃቱ የተሰነዘረው በወታደራዊ ሥፍራ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አንድ ዓመት ሊደፍን አስር ቀናት ያህል የሚቀረው የትግራዩ ጦርነት ከሰሞኑ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡