Sunday, September 22, 2024
spot_img

አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ፓርቲያቸው አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 11፣ 2014 ― በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት በደረሰባቸው ድብደባ ሰበብ ችሎት ሳይገኙ መቅረታቸውን ፓርቲያቸው በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ አሳውቋል፡፡

ፓርቲው እንገደለጸው ከሆነ ዛሬ ጧት በነበረው ውሎ አንደኛው ተከሳሽ ስንታየሁ ቸኮል ባቀረቡት ሪፖርት አቶ እስክንድር ነጋ በትናንትናው እለት ምሽት እስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት በችሎቱ ሊገኙ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

የአቶ ስንታየሁ ሪፖርት እንደተሰማ የእነ እስክንድርን ችሎት ለመከታተል የመጡት ታዳሚዎች ተቃውሞ በማሰማት ችሎቱን አቋርጠው መውጣታቸውን እና ችሎቱ መቋረጡንም የባልደራስ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ ነግረውኛል ብሎ አዲስ ዘይቤ ዘግቧል፡፡

አቶ እስክንድር ላይ የደረሰውን ድብደባ መንስዔ እና ተጠያቂ አካላቱን ጉዳይ ለማጣራት ጠበቃዎቹ ወደ እስር ቤት መሄዳቸውን የገለፁት ኃላፊው፣ ችሎቱን አቋርጠው የወጡት ታዳሚዎች በፖሊስ ተይዘው ወደ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

ባልደራስ በገጹ ባሰፈረው መረጃ፣ አቶ እስክንድር በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ጉልበታቸው መቁሰሉን ዋና ሳጅን መስፍን ይልማ የተባሉ የቂሊንጦ ወህኒ ቤት የፈረቃ ሓላፊም ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

በዛሬው እለት ሊካሄድ የነበረው የመዝገቡ በተከታታይ ምስክር የመስማት ሂደት በትላንትናው እለት የጀመረ ሲሆን፣ በእለቱ በነበረው ምስክርነት ዐቃቤ ሕግ ካቀረባቸው መካከል ይባስ አሰፋ የተባለ ነፍስ ማጥፋትን ጨምሮ ከፍተኛ ወንጀሎች የፈጸመ የህግ ታራሚ የሆነ ግለሰብ እንደሚገኝበት ተነግሯል፡፡ ግለሰቡ ከዚህ ቀደም የአሁኑ የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት ድብደባ መፈጸሙ ይነገራል፡፡

በዛሬው እለት ሊካሄድ የነበረው የምስክር አሰማም ሂደት ተሰርዞ፣ ለፊታችን ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 ተዘዋውሯል፡፡

የባልደራስ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የፓርቲው ሰዎች የሓጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከአንድ ዓመት ለተሻገረ ጊዜ በእስር አሳልፈዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img