አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 11፣ 2014 ― በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በሰሜን ጎንደር ዞን አዳርቃይ ወረዳ ዛሪማ ከተማ የሚገኘውን መስጂድ ማውደሙን የክልሉን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሐጂ ሙሐመድ ሐሰንን ጠቅሶ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡
ሐጂ ሙሐመድ ውድመት የደረሰበት መስጂድ ታሪካዊ እና በቅርቡ በሕዝብ ሃብት እድሳት የተደረገለት ነው ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሕወሃት በርካታ መስጂዶችን እንዳወደመ መረጃዎች እየወጡ ነው ያሉት ሐጂ ሙሐመድ፣ በቀጣይም ጉዳት የደረሰባቸው ተለይቶ ትውልዱ የቡድኑን የጥፋት ልክ በውል እንዲገነዘብ ይደረጋል ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡ ዋና ጸሐፊው አክለውም ሕወሃት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩ ተማሪዎችንም ጨፍጭፏል ብለዋል፡፡
አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት የቀረው በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት በርካታ የእምነት ሥፍራዎች መውደማቸው ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡