Sunday, September 22, 2024
spot_img

በትግራይ ክልል የባንክ ሂሳብ ያላቸው ደንበኞች ላይ የተጣለው እገዳ መነሳቱ ተሰማ

በትግራይ ክልል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባንክ ሒሳብ ከፍተው ከጦርነቱ በኋላ ሂሳባቸው የታገደባቸው ደንበኞች አሁን እገዳው እንደተንሳላቸውና ሂሳባቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ መፈቀዱ ተሰምቷል፡፡

አንድ ዓመት ሊደፍን የተቃረበው የትግራይ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ በትግራይ ክልል ያለው የባንክ አገልግሎት ሲቋረጥ በትግራይ ክልል የተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች እንደይንቀሳቀሱ አብረው ታግደው ነበር፡፡ ለእገዳው ምክንያት የነበረው ከፀጥታ ስጋት ጋር የተያያዘ የገንዘብ ዝውውርን መግታት መሆኑ በወቅቱ ተጠቅሷል፡፡

ዋዜማ ራድዮ አንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊ ነግረውኛል እንዳለው፣ ትግራይ ክልል ሂሳብ የከፈቱ ደንበኞቹ የታገደባቸውን ሂሳብ ለማንቀሳቀስ ከፈለጉ አቅራቢያቸው ባለ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ቀርበው የታገደባቸውን ሂሳብ ማንቀሳቀስ እንዲፈቀድላቸው የሚጠይቅ ማመልከቻ በመጻፍና ከማመልከቻው ጋርም ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያን እንዲሁም የሂሳብ ደብተራቸውን በማያያዝ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ባንኩም አስፈላጊውን ማጣሪያ አድርጎ ደንበኞቹ ሂሳባቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ያደርጋል፡፡

ትግራይ ክልል ተከፍተው በጦርነቱ ሳቢያ መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሂሳቦችን እንዲንቀሳቀሱ የማድረጉን ስራ ግን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጭ ሁሉም የግል ንግድ ባንኮች ስለመጀመራቸው ማረጋገጥ አልተቻለም የተባለ ሲሆን፣ የአንድ የግል ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ስለ ጉዳዩ መረጃ እንደሌላቸው መናገራቸውም ተጠቅሷል፡፡

በፌዴራል መንግስትና በህወሀት መካከል የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ባንኮች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በክልሉ ባሉ የሁሉም ባንኮች ቅርንጫፎች የተከፈቱ ሂሳቦች መታገዳቸው በርካቶችን ለችግር ዳርጓል። በትምህርትም ሆነ በስራ አጋጣሚ ትግራይ ክልል ኖረው እዛው የባንክ ሂሳብ ከከፈቱ በኋላ መኖርያ እና መስሪያ ቦታቸውን የቀየሩ ግለሰቦች የባንክ ሂሳባቸው መታገዱ ያላቸውን ገንዘብም ሆነ የወር ደሞዛቸውን ሳይቀር ማንቀሳቀስ አቅቷቸው ተቸግረዋል ቆይተዋል። ብዙዎችም ገንዘብን ለማንቀሳቀስ ሌላ የባንክ ሂሳብ ማውጣትንም እንደ አማራጭ ወስደዋል።

የፌዴራል መንግስት ጦር ክልሉን ለቆ ከወጣ በሁዋላ ክልሉን በጊዜያዊነት ሲያስተዳድሩ በነበሩ ሰራተኞች የተጻፉ ቼኮች እንዳይመነዘሩ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትእዛዝ መሰጠቱም ተነግሮ ነበር።

ንግድ ባንክ ትእዛዙን ያስተላለፈው የፌዴራል መንግስት በሰኔ ወር 2013 በተናጠል አውጄዋለሁ ያለውን የተኩስ አቁም ተከትሎ መቀመጫውን አዲስ አበባ ካደረገው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ደረሰኝ ባለው ደብዳቤ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ገልጾ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img