የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ያሉ የዕርዳታ ሠራተኞቹን በቅርቡ በግማሽ ለመቀነስ ማቀዱ ተነግሯል፡፡
እንደ አሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ከሆነ ድርጅቱ በክልሉ ያሉትን 530 የዕርዳታ ሠራተኞች ወደ 220 ዝቅ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ድርጅቱ የዕርዳታ ሠራተኞቹን ለመቀነስ ያቀደው፣ በእርዳታ ሥራው ላይ ያሉት እክሎች ባለመፈታታቸው እና የጸጥታው ሁኔታ በማሽቆልቆሉ እንደሆነ ገልጧል።
በትግራይ ክልል አፋጣኝ የእርዳታ አቅርቦት ቢያስፈልግም ባለፉት ጥቂት ወራት ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እጅግ ፈታኝ መሆኑ ይነገራል፡፡ መነሻው ለስምንት ወራት የዘለቀው የሕወሓት ኃይሎች እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጦርነት ሲሆን፣ ግጭቱ አሁን ላይ ዳግም ወደ አጎራባች ክልል አፋር ደርሷል።
በትግራይ ክልል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል የሚለው የተባበሩት መንግሥታት፣ በቅርብ ጊዜያት በተለይ የትግራይ ክልል ይፋዊ ባልሆነ የሰብአዊ እርዳታ እገዳ ስር ይገኛል በማለት በመንግስት ላይ ቅሬታውን ሲያቀርብ ነበር፡፡
የድርጅቱ የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት የያዙ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ እንዲያደርግ ጠይቀው፣ ችግሩንም ‹‹ሰው ሰራሽ ነው፣ መንግሥት እርምጃ ከወሰደ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረው ነበር፡፡
ሆኖም የፌዴራል መንግስት የሰብአዊ እርዳታውን እያስተጓጎለ የሚገኘው ሕወሃት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ሰንብቷል፡፡ ለዚህ ማሳያ በሚል ወደ ክልሉ እርዳታ ጭነው የተጓዙ መኪኖች አለመመለስን እንደ ማሳያ አቅርቦ ነበር፡፡
በሌላ በኩል በቅርቡ የፌዴራል መንግስት ከእርዳታ ጋር በተገናኘ ሰባት የመንግስታቱን ድርጅት ሰራተኞች ከአገር ማባረሩ አይዘነጋም፡፡ መንግስት ሰራተኞቹን ለማባረሩ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የሚል ምክንያት አቅርቧል፡፡ በአንጻሩ የተባበሩት መንግስታት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ‹‹ያልተፈቀደ ቃለ መጠይቆችን›› አድርገዋል ያላቸውን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ማውሪን አቺየንግ መጥራቱ አይዘነጋም፡፡
በመንግሥታቱ ድርጅት አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ መደረጋቸው የተነገረው ኃላፊዋ፣ ‹‹ያልተፈቀደ›› በተባለው ቃለ መጠይቅ ለትግራይ ኃይሎች ርህራሄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል በሚል ነበር፡፡
ከትግራይ እርዳታ ጋር በተገናኘ ባለፈው ሳምንት የተሰበሰቡት የቡድን 7 እና ለጋሽ አገራት በክልሉ የመገናኛ፣ የባንክ እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ እና ወደ ትግራይ የሚወስዱ የትራንስፖርት መስመሮች እንዲሁም የአየር ጉዞ ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እንዲመለስ ተስማምተው፣ በዚህ ረገድ አፋጣኝ ለውጦች ካልተደረጉ የሰብዓዊ ድርጅቶች ሥራቸውን ለመገደብ ወይም ለማቆም እንደሚገደዱ አስታውቀው ነበር፡፡