አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 10፣ 2014 ― በትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ ዳግም ጥቃት እንደተሰነዘረ ሬውተርስ በተማው የሚገኙ የረድኤት ድርጅቶችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በዛሬ እለት ረፋድ 4 ሰዐት ከ30 አካባቢ ተሰንዝሯል የተባለው ጥቃት ቀበሌ 05 በተባለው ሥፍራ በሚገኝ ሲሚንቶ ማምረቻ አካባቢ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በዛሬው እለት ተሰንዝሯል የተባለውን የአየር ጥቃት በተመለከተ በሕወሓት ስር የሚገኘው የክልል መገናኛ ብዙሃን በተመሳሳይ ጥቃቱ ረፋድ ላይ መሰንዘሩን በመጥቀስ ምስሎችን ያጋራ ሲሆን፣ ሬውተርስ በፎቶግራፉ ላይ የተጋሩትን ስፍራዎች የት እንደሆኑ ማረጋገጥ አልቻልኩም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰኞ ጥቅምት 8፣ 2014 በመቀለ ከተማ በተመረጡ ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር፡፡
አየር ኃይሉ ፈጸምኩት ባለው የአየር ድብደባ ህወሓት ይጠቀምባቸዋል ባላቸው የመገናኛ አውታሮችና መሳሪያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንና በጥቃቱ ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉ የተነገረ ቢሆንም፣ በሕወሓት በኩል በጥቃቱ ንጹሐን ተገድለዋል የሚል ክስ ቀርቧል፡፡
የዛሬውን ጥቃት በተመለከተም ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጥም፣ መንግስታዊው የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ መከላከያ ያካሄዳቸው የአየር ድብደባዎችን በተመለከተ የተዛባ ግንዛቤ መኖሩን ጠቁሞ፣ ጥቃቶቹ ኢላማ ያደረጉት የሕወሃት የጦር መሳሪያ ማምረቻ እና የትጥቅ ጥገና ጣቢያዎችን ከጥቅም ውጪ ለማድረግ ነው ብሏል፡፡
አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውና ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ጦርነት ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ከባድ ጉዳትን አስከትሏል።