አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 9፣ 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ የትግራይ ጦርነት ተፋላሚ አካላት ሰላማዊ ሰዎችን እና መሠረተ ልማቶችን ኢላማ ከማድረግ እንዲታቀቡ መጠየቃቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ስቴፋን ዱያሪክ በትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ የአየር ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በኒውዮርክ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ጉቴሬዝ ጥቃቱ መሰንዘሩ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተፋላሚ አካላት ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በትግራይ ክልል መቀመጫ መቐለ ከተማ ትላንት ተሰንዝሯል በተባለው የአየር ላይ ጥቃት ንጹሐን ኢላማ መደረጋቸውን የሕወሃት መገናኛ ብዙሃን የዘገቡ ቢሆንም፣ በመንግስት በኩል የወጣው መረጃ ንጹሐን ኢላማ አልተደረጉም የሚል ሆኗል።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በኩል በተለቀቀው መረጃ መቀሌ ከተማ በሁለት ቦታዎች የተደረገው የአየር ድብደባ ኢላማ የተደረጉት የመገናኛ እና የሚዲያ ማሰራጫ ጣቢያዎች እንደነበሩ ነው የተነገረው።
በሌላ በኩል በዚሁ ጦርነት የሕወሓት ኃይሎች በውጫሌና በአፋር ክልል ጭፍራ አካባቢዎች ላይ በፈጸሙት የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥት አሳውቋል።
የሕወሃት ኃይሎች በነዚህ አካባቢዎች በንጹሐን ላይ አድርሰውታል የተባለውን ጥቃት በተመለከተ የሰጡት ምላሽ የለም።
ከትግራይ ክልል አልፎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት ቀርተውታል።