ደሞዛቸው ተቋርጦባቸው የነበሩ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስዎች ውስጥ ሲያስተምሩ ከነበሩ መምህራን መካከል፣ የራያ እና መቐለ ዩኒቨርስቲ መምህራን ደሞዝ አንደተከፈላቸው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ የትግራይ ክልል ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ላለፉት ኹለትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ወራት ደሞዝ እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ችግር ላይ መሆናቸው ከዚህ ቀደም ተነገሮ ነበር፡፡
መምህራኑ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው በተደጋጋሚ ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተው እስካሁን ያልተከፈላቸውን የወር ደሞዝ መከፈል መጀመራቸውን ተናግረዋል። በትግራይ ክልል የሚገኙት የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች አራት ሲሆኑ፣ ራያ፣ መቐለ፣ አክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርስቲዎች ናቸው።
የአራቱም ዩኒቨርስቲ መምህራን የወር ደሞዝ ባለፉት የክረምት ወራት ሳይከፈላቸው ቢቆይም፣ የራያ ዩኒቨርስቲ መምህራን የሦስት ወር ማለትም ከሰኔ 2013 እስከ ነሐሴ 2014 ደሞዝ የተከፈላቸው ሲሆን፣ የመቐለ ዩኒቨርስቲ መምህራን ደግሞ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ/2014 የኹለት ወር ደሞዝ ተከፍሏቸዋል ነው የተባለው።
የወር ደሞዝ ከፍያው የተቋረጠው በአራቱም ዩኒቨርስቲዎች ቢሆንም፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የአክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርሰቲ መምህራን የተቋረጠባቸው ደሞዝ እንዳልተከፈላቸው እና በሒደት ላይ እንዳለ ለማወቅ መቻሉን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ዩኒቨርስቲዎቹን በበላይነት ሲያስተዳደር የነበረው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከመስከረም ወር ጀምሮ መምህራን በአካል በመገኘት አቴንዳንስ ትፈርማላችሁ እንደተባሉ መምህራኑ ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ደሞዝ የተከፈላቸው መምህራን የመስከረም ወር ግን ገና እንዳልተከፈላቸው ጠቁመዋል። የተቋረጣባቸው ደሞዝ የተከፈላቸው የራያ እና መቐለ ዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የጠየቃቸውን ማስረጃዎችና መስፈርቶች ቀድመው በማሟላታቸው መሆኑ ተገልጿል።