Thursday, November 21, 2024
spot_img

ለትግራይ ጦርነት መፍትሔ ለማበጀት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ከሕወሓት ውጪ ያሉ የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎችን ማሳተፍ እንደሚኖርበት ሦስት የትግራይ ፓርቲዎች አሳሰቡ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 6፣ 2014 ― በትግራይ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ባይቶና፣ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ እና ሳልሳይ ወያነ ለትግራይ ጦርነት መፍትሔ ለማበጀት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ከሕወሓት ውጪ ያሉ የትግራይ ክልል የፖለቲካ ኃይሎችን ማሳተፍ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ባወጡት መግለጫ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ በትግራይ ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል የተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸውን ደግፈዋል፡፡ በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ጋር ተመሳሳይ አቋም ማንጸባረቁን አድናቆት ቸረውታል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው ወር መጀመሪያ የፈረሙት ዕቀባ ግጭቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ ተኩስ አቁሙን የተከላከሉ በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑ ወይም ተባባሪዎቻቸው ላይ ያነጣጠረ መሆኑ መነገሩ ይታወሳል።

የባይደንን ትእዛዝ የደገፉት ፓርቲዎቹ በጋራ መግለጫቸው በትግራይ እየተካሄደ የሚገኘውን ጦርነት በሕዝቡ ላይ የሚደረግ ‹‹ጭፍጨፋ›› እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ እስካሁን መሬት ላይ ተግባራዊ የተደረገ ተጨባጭ እርምጃ አልወሰደም ያሉት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ጉዳዩን ለማስቆም ቀዳሚ እርምጃው ሊሆን የሚገባው ተፈጽሟል ያሉትን ድርጊት በትክክለኛ ስሙ መጥራት ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

መግለጫውን ያወጡት ሦስቱ ፓርቲዎች በፌዴራል መንግስት ሕገ ወጥ ነው የተባለውና በ2011 ጳጉሜን ወር በትግራይ በተካሄደው ምርጫ ተሳታፊ የነበሩ ናቸው፡፡ ከፓርቲዎቹ መካከል ባይቶና በወቅቱ አሸናፊ ነበር ከተባለው ከሕወሃት የተረፈውን ብቸኛ ወንበር አግኝቶ ነበር፡፡

አንድ ዓመት ሊደፍን ሦስት ሳምንታት የቀሩት የትግራይ ጦርነት ባላፉት ቀናት አገርሽቶ መቀጠሉን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረትን የመሳሰሉ አካላት የጦርነቱ ተፋላሚዎች ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን ቢያቀርቡም ጦርነቱ ተባብሶ መቀጠሉ ነው የሚነገረው፡፡

ከሰሞኑ ላገረሸው ውጊያ የሕወሃት ኃይሎ በቀዳሚነት የአገር መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ኃይሎችን ሲከሱ፣ መከላከያ ሚኒስቴር ዘግየት ብሎ ባወጣው መግለጫ እንደ አዲስ ተጠናክሮ ቀጥሏል የተባለውን ጦርነት ከባለፈው ሰኞ ጥቅምት 1፣ 2014 አንስቶ የከፈተው ሕወሓት ራሱ ነው ብሏል፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img