Sunday, September 22, 2024
spot_img

በደሴ ከተማ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸውን ትምህርት ቤቶች ለማደስ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል ተባለ

ከ300 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባት ደሴ ከተማ 22 ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መጠለያ በመሆናቸው በወቅቱ ትምህርት ማስጀመር አለመቻሉን የከተማው ትምህርት መምሪያ አስታውቋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ እያሱ ዘውዱ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማታቸው በመውደሙ ትምህርት ቤቶቹን ለመማር ማስተማር ሥራ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠይቅ ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

ኃላፊው ‹‹በትምህርት ቤቶቹ የውሃና የመብራት ዝርጋታዎች ወድመዋል፤ ወንበሮች፣ መስኮቶች፣ በሮች ተሰባብረዋል፣ መጸዳጃ ቤቶች ተደርምሰዋል፤ ክፍሎቹ ምግብ ማብሰያ በመሆናቸውም ቀለማቸው ተለውጧል፤ አጥራቸውም ቢሆን ተሰባብሯል›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

በዚህ ላይ በተካሄደ ጥናትም ትምህርት ቤቶቹን ወደ ቀደመው ሁኔታቸው ለመመለስ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ አቶ እያሱ ገልጸዋል።

እንደ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እያሱ ከሆነ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም በከተማዋ ትምህርት ለማስጀመር በሚሊሻ እና መከላከያ ማረፊያነት የተያዙ አስር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተለቅቀው በአምስቱ ከሰኞ ጥቅምት 1፣ 2014 ጀምሮ ለ2013 12ኛ ክፍል ተፈታኞች የክለሳ ትምህርት ተጀምሯል ብለዋል።

የ2014 የ12ኛ ክፍል ተፈታኞችን ትምህርትም የፊታችን ሰኞ ጥቅምት 8፣ 2014 ለመጀመር ክፍሎችን የማጽዳት እና ወንበሮችን የማደስ ሥራ መጀመሩን ኃላፊው ገልጸዋል።

በከተማዋ 12 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖሩን የገለፁት ኃላፊው፤ ከተለቀቁት ውጭ ባሉት ሁለተኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመርም ለተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያ ለማዘጋጀት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

‹‹ገራዶ ላይ 25 ድንኳን ተተክሏል። የግልና የአነስተኛና ጥቃቅን ሼድ፣ ስምንት የግል ሼዶችን ለጊዜያዊ መጠለያነት ለመጠቀም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሠራን ነው›› ብለዋል።

አቶ እያሱ አክለውም አነስተኛ እና ጥቃቅን የማይሰሩባቸውንና በዓለም ባንክ የተሰሩትን ሸዶች ቁልፍ መረከባቸውን ተናግረው፤ መጠለያው ለተፈናቃዮቹ ከተዘጋጀ በኋላ ጥቅምት 15፣ 2014 ትምህርት ለመጀመር ማቀዳቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ ይህ የሚሆነው ግን የጊዜያዊ መጠለያ ግንባታው ሲሳካ ነው›› ሲሉ ኃላፊው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶቹ ከ20 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፤ ርብርብ ካልተደረገ በስተቀር እየተዘጋጀ ያለው መጠለያም በቂ አለመሆኑን አመልክተዋል።
እንደ አቶ እያሱ ከሆነ በደሴ ከተማ በዚህ ዓመት 57 ሺህ 500 የሚሆኑ ተማሪዎችን ለማስተማር የታቀደ ሲሆን፣ ተፈናቃይ የሆኑ 800 ተማሪዎችም ለመማር ተመዝግበዋል።

ከደሴ በተጨማሪም በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው ኮምቦልቻ ከተማም ከ5 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በ12 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጀ አማረ አስታውቀዋል።

አቶ ደረጀ እንዳሉት በእነዚህ ትምህርት ቤቶችም ሆነ በከተማዋ ባሉ የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርት አልተጀመረም።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ቢያዝን በክልሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ክትምህርት ገበታቸው እንደቀሩ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።

በጦርነቱ ምክንያትም 277 ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን፤ ከ1 ሺሕ 300 በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ ደግሞ በከፊል ጉዳት መድረሱን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img