አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 5፣ 2014 ― ሦስተኛው ዓመታዊ የዲጂታል ጥራት የሕይወት ጠቋሚ ጥናት ኢትዮጵያ ከ110 አገራት ውስጥ የመጨረሻን ደረጃ መያዟን አመልክቷል፡፡
የዲጂታል ጥራት የሕይወት ጠቋሚ ጥናት በሳይበር ደህንነት ኩባንያው ሰርፍሻርክ የሚካሄድ ሲሆን፣ በአምስት መሠረታዊ የዲጂታል ደኅንነት ምሰሶዎች ላይ በመመርኮዝ አገሮችን የሚገመግም ነው፡፡
በዚሁ ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካተተችው ኢትዮጵያ፣ በተያዘው ዓመት በበይነ መረብ ተመጣጣኝነት 104ኛ፣ በበይነ መረብ ጥራት 110ኛ፣ በኤሌክሮኒክ መሠረተ ልማት 110ኛ፣ በኤሌክትሮኒክ ደህንነት አጠቃቀም 107ኛ እና በመንግስታዊ አገልግሎቶች የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ዘርፍ 107ኛ በመሆን በንጻሬ ዝቅተኛ ውጤቶችን አስመዝግባ በድምር ውጤት ከአገራቱ መካከል መጨረሻ ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያ በጥናቱ ከተካተቱት አገራት መካከል ከዛምቢያ ጋር ተመሳሳይ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ ያላት ቢሆንም፣ የሁለቱ አገራት የዲጂታል ሕይወት ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ ተለያይቶ ዛምቢያ 94ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
በሌላ በኩል የሰርፍሻርክ ጥናት አገራትን በቀጣና ደልድሎ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት በአሜሪካ ምድብ ዩናይትድ ስቴትስ ቀዳሚ ሆናለች፡፡ በእስያ ምድብ ደግሞ ደቡብ ኮሪያ በአንደኝነት ስትቀመጥ፣ ከአፍሪካ አህጉር ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በኦሺኒያ ምድብ ደግሞ አውስትራሊያ ከፊት ተቀምጣለች፡፡
🤔