የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሚኒስቴር ሕወሓት በሁሉም ግንባሮች ከሰኞ ጥቅምት 1፣ 2014 ጀምሮ ውጊያ እንደከፈተ ትላንት ምሽት በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ በለቀቀው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብሎ የቆየ የመሰለው በሰሜን ኢትዮጵያ በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በሕወሃት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ዳግም ማገርሸቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡
የሕወሓት ኃይሎችም በተለያዩ አመራሮቻቸው በኩል በሁሉም ግንባሮች መከላከያ ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ከፍቶብናል ሲሉ ቢደመጡም፣ ከፌዴራል መንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ አልነበረም፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው፣ የሕወሓት ኃይሎችን በራሱ በመከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጥምረት ‹‹ከባድ ኪሳራ እያደረሰና ሽንፈት እያከናነበ›› እንደሚገኝ ነው የገለጸው፡፡ አክሎም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቋል፡፡
ባለፉት ቀናት አገርሽቷል የተባለው ውጊያ በአፋር እና በአማራ ክልል ቀጥሎ ሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ አቅራቢያም እየተደረገ መሆኑ ከሕወሃት በኩል ተነግሯል። በዚሁ ውጊያ በአፋር ክልል ፈንቲ ዞን በምትገኘው አውራ ከተማ የሕወሓት ኃይሎች በንጹሐን ላይ ማክሰኞ ጥቅምት 2፣ 2014 ጥቃት ሰንዝረው በርካቶችን መግደላቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ የረድኤል ድርጅቶችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ነገር ግን ጥቃቱን ሰንዝሮ ንጹሐንን ገድሏል የተባለው ሕወሃት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በአካባቢው ንጹሐንን ገድላዋል መባሉን አስተባብለዋል።
በሌላ በኩል ከሰሞኑ ውጊያው ማገርሸቱን ተከትሎ የሕወሃት ቃል አቀባይ የሆኑት ፍሰሃ አስገዶም ከመንግስት ጋር ለመደራር ዝግጁ ነን ሲሉ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ተናግረዋል፡፡ ከሚድያው ጋር በነበራቸው ቆይታ ማን ያደራድር የሚለው ሁለተኛ ጉዳያችን ነው ያሉት ፍስሃ አስገዶም፣ ‹‹ለመደራደር ቁርጠኛ ነን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በቀደመው ጊዜ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ የነበሩት ፍስሀ፣ በአሁኑ ጊዜ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከአማራ ክልል ኃይሎች ጋር በመሆን በጦር ጄት፣ በድሮን፣ በታንክና በሌሎችም ከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ጥቃት እየተፈጸመብን ስለሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንድ ነገር ያድርግ ሲሉም ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡
የሕወሃት ጦር አዛዥ ጀኔራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ በበኩላቸው ረቡዕ መስከረም 3፣ 2014 ለኒውዮርክ ታይምስ በሕወሃት እና መከላከያ ሠራዊት መካከል ሰሞኑን የተጀመረው ውጊያ በቀናት ወይም ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል። ጦርነቱ ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ አንድምታ ይኖረዋል ያሉት ጻድቃን፣ ጎረቤት አገር ኤርትራ ትልቅ ወታደራዊ ስጋት እንደሆነችባቸው የጠቀሱ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ኤርትራን እንዲያስታግስላቸው ጠይቀዋል።
በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሃት ኃይሎች መከከል የሚካሄደው ጦርነት ከሦስት ሳምንታት በኋላ አንድ ዓመት ይደፍናል።