Saturday, November 23, 2024
spot_img

የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ላይ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥ አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 5፣ 2014 ― የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ በአሜሪካው የቀረጥ ነጻ ንግድ (አጎዋ) ባላት ተጠቃሚነት ላይ በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥ የአሜሪካ የንግድ ኃላፊ ካትሪን ታይ ተናግረዋል ሲል ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ 237 ሚሊዮን ዶላር ምርት አጎዋን በመጠቀም ያለ ቀረጥ ወደ አሜሪካ ልካለች፡፡ ነገር ግን አሜሪካ መንግሥት የትግራዩን ሰብዓዊ ቀውስ አልፈታም በሚል ዕድሉን ከኢትዮጵያ ላይ እነጥቃለሁ ስትል እየዛተች ቆይታለች፡፡

በተመሳሳይ ይህንኑ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመታት በፊት የተሰጣትን ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የሚያደርገውን ‹‹አፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት›› (አጎዋ) ተጠቃሚነት እንድታጣ ለሕወሃት በሎቢ አድራጊነት የሚሠራው ቮን ባተን ሞንቲግዩ የተባለ ድርጅት እየወተወተ ይገኛል፡፡

ግፊቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ዕድሉን ልታጣ ትችላለች በሚል በሰፊው ግምቶች እየቀረቡ የሚገኙ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ማሞ ምሕረቱ ከሰሞኑ ፎሬን ፖሊሲ መጽሔት ላይ በጻፉት መጣጥፍ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነት እንዳያግድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፖሊሲ አማካሪው አሜሪካ በኢትዮጵያ ጸጥታ ሁኔታ ላይ ቅሬታ ቢኖራትም፣ ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነቷ ማገዷ አጣብቂኝ ውስጥ ባለው የሀገሪቱ አምራች ዘርፍ ሕልውና ላይ ከባድ አደጋ ይደቅናል የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ አያይዘውም እገዳው ከተጣለ ከትግራዩ ግጭት ጋር አንዳችም ግንኙነት በሌላቸው ተራ ኢትዮጵያዊያን ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ባልደረባ የሆኑት ቢልለኔ ሥዩም ጉዳዩን በተመለከተ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሴቶች የሥራ ዕድል በማሳጣት፣ ሰብዓዊ ቀውስን ማስቆም አይቻልም ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለይ አጎዋን ተስፋ አድርገው የመጡ ባለሀብቶችና የኢንዱስትሪ አልሚዎች፣ ይህ ተጠቃሚነት ቢሰረዝና ከአገር ቢወጡ ተመልሰው መምጣታቸው በጣም ከባድ እንደሚሆን ባለሞያዎች ይገልጻሉ፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ ከአጎዋ ብትሰረዝ አገር ውስጥ የሚገኙት እንደ ካልቪን ክለይን፣ ቶሚ ሂልፊገር እና ኤችኤንድኤምን የመሳሰሉ በዓለም ታዋቂ አምራቾች መቆየታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ስለመሆኑም ስጋታቸውን የሚያጋሩ አሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img