አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 4፣ 2014 ― መንግሥት ከቱርክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወይም ድሮኖች ለመግዛት ጥያቄ አቅርቦ አገሪቱ ሳትሸጥ እንዳልቀረች ሬውተርስ የዜና ወኪል ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ነግረውኛል ብሎ ዘግቧል፡፡
መንግሥት ከቱርክ ሊገዛ ጥያቄ አቅርቧል የተባለው ባይራክታር ቲቢ2 የተባለውን ዐይነት ሲሆን፣ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሞሮኮም ጥያቄውን መቅረቧን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ የተጠቀሰውን ድሮን ለመግዛት ያቀደችው ከነ መለዋወጫው መሆኑም ነው በዘገባው የሠፈረው፡፡
በጉዳዩ ላይ የዜና ወኪሉ አናገርኳቸው ያላቸው ዲፕሎማት ሞሮኮ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ይቅረብልኝ ያለችው ይህንኑ ድሮን በመጀመሪያ ዙር የተረከበች ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ለመቀበል እቅድ መያዟን ቢገልጹም ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ግን ብዙም ግልጽ አለመሆኑን መናገራቸው ተገልጧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ምን ያህል ድሮኖችም እንዳዘዘችና የዋጋ ዝርዝሩን በተመለከተም የተገለጸ ነገር አለመኖሩ በዘገባው ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከቱርክ ማዘዟ ከተነገረው ድሮን ጋር በተገናኘ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበው ግብጽ፣ አሜሪካን እና ጥቂት የአውሮፓ አገራትን ስምምነቱ እንዲቀር እንዲረዷት መጠየቋ ነው የተነገረው፡፡
ድሮኖቹን በተመለከተ ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ ወር ወደ ቱርክ ባቀኑበት ወቅት ሁለቱ አገራት በውሃ ልማትና በመከላከያ ዘርፎች ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተነሳ ወዲህ የፌደራሉ መንግሥት በሕወሓት ኃይሎች ላይ ድሮኖችን ስለመጠቀሙ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች በስፋት ሲወጡ ቆይተዋል። ከሰሞኑ ባገረሸው ጦርነትም ቢሆን የሕወሃት ኃይሎች የፌዴራሉ መንግስት ጥቃቱን እየተሰነዘረብን ነው ብለው ከጠቀሷቸው መካከል ድሮኖች ይገኙበታል፡፡