አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 4፣ 2014 ― በአማራ ክልል ደሴ ከተማ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ለሚገኘው ጦርነት መዋጮ አልሰጣችሁም የተባሉ የንግድ ሱቆች መታሸጋቸው ተሰምቷል፡፡
ይህንኑ ለአምባ ዲጂታል የተናገሩ ነጋዴዎች ያረጋገጡ ሲሆን፣ በሱቆቹ ላይ ‹‹ለሕልውና ዘመቻ ድጋፍ ባለማድረግዎ ታሽጓል›› የሚል ወረቀት እንደተለጠፈባቸው ተመልክተናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የታሸጉት የንግድ ሱቆች ቀድሞ በነበሩ ቀናት ‹‹ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅብዎትን ድጋፍ ባለማድረግዎ ለሁለት ቀናት ውስጥ የሚጠበቅብዎትን ገንዘብ ገቢ በማድረግ ደጀንንትዎን በተግባር እንዲያረጋግጡ በአማራ ሕዝብ ስም በጥብቅ እንጠይቃን›› የሚል ማሳሰቢያ ተለጥፎባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ በዚሁ ከተማ ሌሎች ደግሞ እንዲሰጡ የተጠየቁትን ገንዘብ ከፊሉን በማስገባታቸው ቀሪውን ገቢ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል ነው የተባለው፡፡
በደሴ ከተማ መዋጮ አልሰጣችሁም የተባሉ የንግድ ሱቆች መታሸጋቸውን በተመለከተ ሱቆቹ ለምን ያህል ጊዜ ታሽገው እንደሚቆዩና ተያያዥ ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ የከተማው አስተዳዳር የሠጠው ይፋዊ ማብራሪያ የለም፡፡ ሱቃቸው የታሸገባው ነጋዴዎች የሚመለከተው የመንግስት አካል በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
መዋጮ አልሰጣችሁም በሚል ሱቆች የታሸጉባት የደሴ ከተማ፣ የሕወሃት ኃይሎች ወደ አማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች መግፋታቸውን ተከትሎ ከሰሜን ወሎ እና አጎራባች አካባቢዎች የተፈናቀሉ በርካታ ሺሕ ዜጎችን እያስተናገደች የምትገኝ ናት፡፡
በአሁኑ ጊዜ በከተማው ውስጥ 14 የተፈናቃዮች የመጠለያ ካምፖችና ትምህርት ቤቶች እነዚህን የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ በካምፖቹ ውስጥ ከህጻን እስከ አዋቂ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በርካታ ህጻናት፣ ወላድና ነፍሰ ጡር እናቶች አሉበት። እነዚህን ተፈናቃዮች ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የከተማው ነዋሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው በሚል በሙገሳ ሲነሱ ሰንብቷል፡፡
ከ 500 መቶ ሺህ በላይ ስደተኞችን ያለምንም የመንግስትና አለማቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች ተሳትፎ ብቻውን አስጠልሎ እየመገበ ያለን የማህበረሰብ ክፍል ለኛ በእጃችን ጥሬ ገንዘብ ካልሰጠህ ብሎ እንዲህ አይነት አሰነዋሪ ስራ የሚሰራ የመንግስት አካል ያለበት ሀገር ወሎ ላይ ብቻ ይመስለኛል