አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 3፣ 2014 ― የቡድን 7 አባል አገራት እና ሌሎች ለጋሽ አገራት በትግራይ ግጭት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ተሳታፊዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጭዎች እና ዓለም አቀፍ ለጋሾችን ለሚያጋጥማቸው ውስብስብ ችግሮች ፈጣን መፍትሔዎችን ለመፈለግ እና እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን ከግምት ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል ብሏል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ የካናዳ፣ ዴንማርክ፣ የፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ተወካዮች ተሳታፊ እንደነበር የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት አስተባባሪ ሰማንታ ፓወር ገልጸዋል፡፡
በስብሰባ ላይ የተሳተፉ ለጋሾች በትግራይ ክልል የመገናኛ፣ የባንክ እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ እና ወደ ትግራይ የሚወስዱ የትራንስፖርት መስመሮች እንዲሁም የአየር ጉዞ ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እንዲመለስ መስማማታቸውም ነው የተገለጸው፡፡ አገራቱ ባለፉት ሁለት ወራት በመንግሥት ታግዷል ያሉትን የነዳጅ፣ መድኃኒቶች እና የህክምና አቅርቦቶችን መፍቀድ እንደሚያካትትም ተስማምተዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ረገድ አፋጣኝ ለውጦች ካልተደረጉ የሰብዓዊ ድርጅቶች ሥራቸውን ለመገደብ ወይም ለማቆም እንደሚገደዱ ያስታወቁት አገራቱ፣ የጤና ተቋማትም ከህክምና አቅርቦት ውጭ እንደሚሆኑ ስጋታቸውን አጋርተዋል፡፡
የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት ባወጣው መረጃ በትግራይ እስከ 900 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች ረሃብን በመሰለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ሰዎች ምግብ ሳያገኙ ለቀናት በመቆየታቸው ቅጠል መብላት ጀምረዋል ሲል አስታውቋል።
ለጋሽ አገራት እና የቡድን 7 አገራት የነዳጅ፣ መድኃኒቶች እና የህክምና አቅርቦቶችን አግዷል የሚል ውንጀላ በመንግስት ላይ ቢያቀርቡም፣ በመስከረም የመጀመሪያ ቀናት መንግስት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የሚቀርቡ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማቀላጠፍ በሚል የፍተሻ ኬላዎች ቁጥር ከ7 ወደ 2 ዝቅ እንዲል መደረጉን የገለጸ ሲሆን፣ የእርዳታ ተቋማት ግን እናሰማራለን የሚሉት የተሽከርካሪዎች ቁጥር ጭማሪ አለማሳየቱን አሳውቆ ነበር፡፡