Monday, September 23, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት ከትግራይ ጦርነት ጋር በተገናኘ ሁለተኛዋን የኢትዮጵያ ኃላፊ መጥራቱ ተሰማ

 

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 3 2014 ― ከትግራይ ጦርነት ጋር በተገናኘ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ማውሪን አቺየንግን እረፍት እንዲወጡ ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከዚሁ ጦርነት ጋር በተገናኘ ያልተገባ አስተያየት ሰጥተዋል ያላቸውን ሁለተኛዋን የድርጅቱን የኢትዮጵያ ኃላፊ መጥራቱ ተሰምቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠርቷቸዋል የተባሉት ሁለተኛዋ ኃላፊ የዩኤንኤፍፒኤ የኢትዮጵያ ኃላፊ ዴኒያ ጌይል መሆናቸውን የፈረንሳዩ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት ቀድሞ የጠራቸውን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ማውሪን አቺየንግ ላይ ውሳኔ ለማሳለፉ ‹‹ያልተፈቀደ ቃለ መጠይቆችን›› አድርገዋል በሚል ምክንያት ማቅረቡ ተነግሮ የነበረ ሲሆን፣ ኃላፊዋ ለትግራይ ኃይሎች ርህራሄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ የዩኤንኤፍፒኤ ኃላፊዋም እንደ የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊዋ ሁሉ ለትግራይ ኃይሎች ርህራሄ አላቸው ባሏቸው የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገናል ስለማለታቸው ዘገባው አመልክቷል፡፡

የኒኳራጉዋ መሠረት ያላቸው ዴኒያ ጌይል የዩኤንኤፍፒኤ የኢትዮጵያ ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት አምና በዚህ ወቅት ነበር፡፡

አሁን እረፍት የተባሉት ማውሪን አቺየንግና እና ዴኒያ ጌይል የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ሕግ ማስከበር ሲል የሚጠራውን ዘመቻ በመደገፍ በርካታ መጣጥፎችን ለሚጽፈው ጄፍ ፒርስ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ መስጠታቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡

በቃለ መጠይቁ ላይ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ አዲስ አበባ የገቡ የተባበሩት መንግሥታት የሥራ ባልደረቦቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመተቸት መሬት ላይ ያሉ የድርጅቱ ተወካዮችን አግልለዋል ማለታቸው ሲነገር፣ ሕወሓትንም ‹‹ቆሻሻ›› እና ‹‹ጨካኝ›› በማለትም ሲሳደቡ እንደሚሰማም ነው የተገለጸው።

ይህንኑ ተከትሎም ሰኞ እለት የአይኦኤም ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ የኃላፊዋን አስተያየቶች አስመልክቶ ደብዳቤ መጻፋቸው የተነገረ ሲሆን፣ ‹‹በድምፁ ላይ በድርጅቱ አባል የተሰጡት አስተያየቶች ከአይኦኤም መርሆች እና እሴቶች ጋር አይዛመዱም፣ በምንም መልኩ የድርጅቱ አቋም እንደተገለጸ ተደርጎ መታየት የለበትም›› ብለው ነበር፡፡

በተለይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቀድሞ እረፍት ይውጡ የመባላቸው ዜና የተሰማው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ማውሪን አቺየንግ ጉዳይ የተለያዩ አስተያየቶችን አስተናግዷል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየት ከሰጡት መካከል የሆኑት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ሥዩም ውሳኔውን ‹‹በጣም የሚረብሽ ነው›› ብለውታል፡፡ አያይዘውም ‹‹በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ያለው ውስጣዊ እና የውጭ ተፅእኖ ፓለቲካ በጥልቀት መመርመር›› እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ መንግስት በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል ያላቸውን ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ማባረሩም በተመሳሳይ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img