Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሕወሓት በሁሉም ግንባሮች ጥቃት ተከፍቶብኛል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 1፣ 2014 ― በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውና ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ሕወሓት ዛሬ ጥቅምት 1፣ 2014 ማለዳ በሁሉም ግንባሮች በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ክልል ኃይሎች ጥቃት ተከፍቶብኛል ሲል ባወጣው መግለጫው አስታውቋል፡፡

ሕወሓት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ የትዊተር ገጽ በኩል ባወጣው መግለጫ፣ ጥቃቱ ድሮንን ጨምሮ በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ በትግራይ ሌላ ዙር እልቂት ከመከሰቱ በፊት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጦርነቱን ያስቁምልኝ ብሏል፡፡

ሕወሓት ጥቃት ተከፍቶብኛል ቢልም በጉዳዩ ላይ ከአገር መከላከያ ሠራዊት በኩል ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡   

ዛሬ በጀመረው የጥቅምት ወር መገባደጃ አንድ ዓመት የሚደፍነው በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው በመከላከያ እና በሕወሃት መካከል የሚካሄደው ጦርነት ባለፉት ሳምንታት ጋብ ያለ መስሎ የነበረ ቢሆንም፣ ዐርብ መስከረም 28፣ 2014 በተመሳሳይ የሕወሃት ቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ ለሬውተርስ የዜና ወኪል የአገር መከላከያ ሠራዊት የአውሮፕላን ድብደባ እያካሄደብን ማለታቸውን ተከትሎ የጦርነቱ ዜና እንደ አዲስ መሰማት ጀምሯል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት በወቅቱ በሕወሃት ቃል አቀባዩ ለቀረበበት ውንጀላ ምላሽ አልሰጠም፡፡

ሬውተርስ ሐሙስ ዕለት ጀምሯል በተባለው ተከታታይ የአየር ጥቃት ትኩረቱን ያደረገው በሦስት አካባቢዎች ላይ ማለትም ከውርጌሳ አቅራቢያ ባለ ቦታ፣ በወገል ጤና እና በምሥራቅ በኩል ደግሞ የአማራ ክልልን ከአፋር ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይ ነው ብሎ ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img