Monday, September 23, 2024
spot_img

በኮሮና ቫይረስ ሰበብ በአንድ ሳምንት ብቻ የ360 ሰዎች ሕይወት አለፈ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 1፣ 2014 ― በኢትዮጵያ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 360 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሰበብ ሕይወታቸውን መነጠቁን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሟቾቹ ቁጥር መበራከት በቅረብ ጊዜያት በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመት ስለመሆኑ የሚነገረው የዴልታ ኮሮና ቫይረስ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያሳወቀው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር እስከ ነሐሴ አጋማሽ ሕይወታቸውን በኮሮና ቫይረስ ካጡት መካከል አንዱ ብቻ ክትባት የወሰደ መሆኑን ያመለከተው የጤና ሚኒስቴር፣ ሌሎች ግን ያልተከተቡ መሆናቸውንና በአገሪቱ የመከተብ ምጣኔም አነስተኛ እንደሆነ ገልጧል፡፡

ከባለፈው እሑድ መስከረም 23 እስከ ትላንት መስከረም 30፣ 2014 ባሉት ስምንት ቀናት በመላ አገሪቱ በኮሮና ቫይረስ የሞቱ ሰዎች 360 ሲሆን፣ ይህም ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡ በየቀኑም በአማካይ ከ1 ሺሕ በላይ በቫይረሱ ሲያዙ፣ በዚህ ሳምንትም በየቀኑ በአማካኝ 44 ሰዎች እየሞቱ እንደሆነም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በወረርሽኙ ዙሪያ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ ክትባት እና ከዛሬ ጀምሮ የሚከፈቱ ትምህርት ቤቶች ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት የሟቾች ቁጥር ማሻቀብ፣ ወደ ፅኑ ህሙማን የሚገቡ ሰዎች ቁጥርና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማንሰራራት ያሳየው የዴልታ ቫይረስ ዝርያ በመኖሩ፣ በስብሰባዎች መበራከት እንዲሁም ማስክ አለማድረግና ውሳኔዎችና ደንቦችን ማክበር በመቀዛቀዙ ምክንያት ነው፡፡

ዶክተር ሊያ ከትምህርት ቤቶች መከፈት ጋር ተያይዞም መምህራንን መክተብ፣ ወላጆችንና ተማሪዎችን መከላከያ ዘዴዎችን ማስተማር፣ ማስክን አስገዳጅ ማድረግ እንዲሁም አካላዊ ርቀትን መጠበቅና የፈረቃ ስርዓትም ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።

ሚኒስትሯ የየበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ)ን ጥናት ዋቢ አድርገው እንዳስረዱት ያልተከተቡ ሰዎች ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭ እንደሆኑና በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ከ4 ነጥብ 5 እጥፍ በላይ፣ ሆስፒታል የመግባት እድላቸው ከ10 እጥፍ በላይ፣ ታመው የመሞት እድላቸው ደግሞ ከ11 እጥፍ በላይ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱ ከተነገረበት መጋት 2012 አንስቶ በአጠቃላይ 5 ሺ 590 ሰዎች ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img