አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 29፣ 2014 ― መስከረም 20፣ 2014 በተካሄደውና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሱን እንዲችል አሊያም ከደቡብ ክልል ጋር እንዲቀጥል በተሰጠው ሕዝበ ውሳኔ አስራ አንደኛው የኢትዮጵያ ክልል ሆኖ የሚቋቋምበትን አብላጫ ድምጽ ማግኘቱን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል።
በደቡብ ክልል ምዕራባዊ አስተዳደር አካባቢዎች በተካሄደው በዚሁ ሕዝበ ውሳኔ ከ98 በመቶ በላይ ድምጽ ሰጭዎች ራሱን የቻለ ክልል እንዲመሠረት እንደደገፉ ነው የተገለጸው።
በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ድምጽ ሰጭዎች ውስጥ 94 በመቶው በሕዝበ ውሳኔው ተሳትፈዋል ነው የተባለው።
በሕዝበ ውሳኔው የተሳተፉት የቤንች ሸኮ ዞን፣ ሸካ ዞን፣ ካፋ ዞን፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና ኮንታ ልዩ ወረዳ ሕዝቦች ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘውን የህዝበ ውሳኔ ውጤት ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደሚያቀርብም ገልጿል።
ምክር ቤቱ የሕዝበ ውሳኔውን የመጨረሻ ውጤት ካጸደቀ፣ ደቡብ ምዕራብ ክልል ተብሎ እንደሚሰየም የሚጠበቀው አዲሱ ክልል፣ የኢትዮጵያ 11ኛው ክልል ይሆናል።