አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 29፣ 2014 ― በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ እስክንድር ነጋና ሌሎች ፖለቲከኞችን ክስ የሚመሩት አቶ ፍቃዱ ፀጋ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተደርገው ተሾመዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሾሙት አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በነሐሴ ወር 2012 አዳዲስ ሹመት በሰጡበት ወቅት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የነበሩት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለዶክተር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ሲያስረክቡ፣ ከአቶ ተስፋዬ ዳባ ጋር በምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግነት ተሹመው ሲገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ መስከረም 24 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚኒስትሮችን ሹመት በሰጡበት ወቅት የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ ወደ ቀድሞ መጠሪያው የተመለሰውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፍትሕ ሚኒስቴር ስያሜ እንዲመሩት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን መሾማቸው ይታወቃል፡፡