አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 29፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ ከተማ ዋና መስሪያ ቤቱ የሚገኘውን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሰብአዊ መብቶች ተሟጋችነት በሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስም እንደሚሰይም አስታውቋል፡፡
ይህንኑ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በዛሬው እለት የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን እረፍት አንደኛ ዓመት መታሰቢያና በሥማቸው የሚጠራውን ፋውንዴሽን ምክንያት በማድረግ በኢንተር ለግዠሪ ሆቴል በተሰናዳ መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ በንግግራቸው ፕሮፌሰር መስፍን፣ የሰብአዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳቦች እንዲታወቁ፣ እንዲሁም በተግባር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደራጀ መልኩ ለሰብአዊ መብቶች ጉዳይ የሚንቀሳቀስ አገር በቀል ድርጅት እንዲቋቋም ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ኮሚሽን የሰየመውን አዳራሽ የምርቃት ሥነ ሥርዐት ወደፊት እንደሚያካሄድ ገልጸዋል፡፡
እውቁ ምሑር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ በ1983 የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን በተቆጣጠረ ማግስት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)ን አቋቁመው በአገሪቱ ውሰጥ ይደረግ የነበረውን የመብት ጥሰት ይፋ በማውጣት ይታወቃሉ፡፡
አሁን የኅልፈታቸውን አንደኛ ዓመት በማስመልክት በቤተሰቦቻቸው እና የቅርብ ወዳጆቻቸው የተቋቋመው በሥማቸው የሚጠራው ፋውንዴሽን በሰብዓዊ መብቶች፣ ርሐብ እና ድህነት ላይ የሚሰሩ ስራዎችን የመደገፍ ዓላማ እንዳለው ተነግሮለታል፡፡
በአስራ ሶስት መስራች አባላት የተቋቋመው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን፤ ከመንግስት፣ ከሃይማኖት፣ ከጎሳ እና ከማንኛውም የፖለቲካ አመለካከት ነጻ በሆነ መንገድ የተመሰረተ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ዘጠኝ አባላት ባሉት ቦርድ የሚተዳደረውን ፋውንዴሽን በዋና ሰብሳቢነት የሚመሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው የቋንቋ እና ሥነ ልሳን መምህር ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ናቸው።
ዶ/ር በድሉ የፋውንዴሽኑን ምስረታ ዕውን ለማድረግ አንድ አመት ጊዜ መፍጀቱን ለሚዲያዎች የተናገሩ ሲሆን፣ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጄንሲ ተመዝግቦ እውቅና ማግኘቱንም ገልጸዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስም የተሰየሙ ቤተ መጽሃፍትን እና ማዕከላትን፤ በሁለተኛ ደረጃ እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲከፈቱ የማድረግ እቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን በድርቅ እና ረሃብ ላይ በሰሯቸው የምርምር ስራዎች ይበልጥ የሚታወቁ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ረሃብ እና ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሐፍትን በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋ አሳትመዋል። በኢትዮጵያ አስከፊ ከሚባሉት የረሃብ ጊዜዎች አንዱ የነበረውን የ1966ቱን ረሃብ በህዝብ ዘንድ እንዲታወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ምሁሩ፤ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰተው ረሃብ ወደ ፖለቲካው ዓለም እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ደጋግመው ይናገሩ ነበር።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለፈው ዓመት መስከረም 20፣ 2013 በ90 ዓመት እድሜያቸው ነበር፡፡