Thursday, November 21, 2024
spot_img

አቶ ታዬ ደንደኣ ወደ ፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ተዛወሩ

የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ታዬ ደንደኣ በሰላም ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ተደርገው በጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አሕመድ ተሾመዋል፡፡

በብልጽግና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነታቸው ወቅት በተለይ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ በሚሰነዝሯቸው አወዛጋቢ አስተያየቶቻቸው የሚታወቁት አቶ ታዬ፣ በቅርቡ በተካሄደው በኦሮሚያ ጨፌ ስብሰባ ላይ ለክልሉ አዲስ መንግስት ምስረታ የቀረቡ እጩዎችን ተከትሎ የሰነዘሩት አስተያየት በመድረኩ ውዝግብ ፈጥሮ እንደነበር መነገሩ አይዘነጋም፡፡

አቶ ታዬ በመድረኩ ላይ እጩዎቹን በተመለከተ ያቀረባቸው ፓርቲው ነው ቢባልም፣ ‹‹እኔ ከአመራሮች መካከል ሆኜ አልሰማሁም›› ሲሉ የተደመጡ ሲሆን፣ ‹‹ፓርቲያችን የሚቀርበውን ነገር እንዴት አናውቅም፣ እንዴት ገሸሽ ሊያደርገን ቻለ›› ሲሉም ጥያቄ ሰንዝረዋል።

በኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ስማቸው ከፊት ከሚጠራ መካከል፣ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቅርበት ካላቸው የፓርቲው ሰዎች የሚሰለፉ ስለመሆናቸው የሚነገርላቸው አቶ ታዬ፣ አዲሱ ሹመታቸው ይፋ የተደረገው በዛሬው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ22ቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ለጽሕፈት ቤታቸው ሚኒስትር ዴኤታዎችን እንዲሁም ለሌሎች ሁለት ተቋማት ኮሚሽነሮችን ባሳወቁበት ወቅት ነው፡፡  

በዛሬው ሹመት፣ ከአቶ ታዬ ደንደኣ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ በዚያው የውጭ ጉዳይ ውስጥ አምባሳደር ብርቱካን አያናን ደግሞ የኃብት ማኔጅመንትና አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አድርገዋል፡፡

በቀደመው ጊዜ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የነበሩት ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በዚያው ሚኒስትር መስሪያ ቤት የፊሲካል ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰዉ

ደግሞ የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተደርገው ተሾመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ውስጥ የነበሩት አቶ ሽሰማ ገ/ስላሴ ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዘዋውረዋል፡፡

የቀድሞው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ ኃላም የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ አቶ ታከለ ዑማ በሚመሩት የማዕድን ነዳጅ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተደርገዋል፡፡

በአዲሱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አወቃቀር ከሚሽንነት ባደገው ፕላንና ልማት፣ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ሲሠሩ የነበሩት ዶ/ር ነመራ ማሞ የፕላን ስታቲስቲክስ እና ፖሊሲ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተደርገው ተሾመውለታል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ንጉሱ ጥላሁን በአዲሱ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ውስጥ የሥራና የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተደርገዋል፤፤

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ብርሃኑ ሌንጂሶን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር

የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አድርገው ኃላፊነት ሰጥተዋል፡፡

የቀድሞዋ የፋና ቴሌቪዥን ዜና መሪዋ ሰላማዊት ካሳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተደርጋ ተሾማለች፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሳሙኤል ሁርቃቶ፣ የፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሲደረጉ፣ ዶ/ር መኩሪያ ሀይሌ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን ኃላፊነት ተረክበዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img