Friday, November 22, 2024
spot_img

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ አመራር አባሏ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሹመት ተሰጣቸው

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 29፣ 2014 ― የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ነብያ መሐመድ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ተደርገው በጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አሕመድ ተሾመዋል፡፡

የነብያ ሹመት ይፋ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለ22ቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታዎችን ዝርዝር ባሳወቁበት ወቅት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነጻነት እና እኩልነት አመራሯ በተጨማሪ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ከእናት ፓርቲ ወ/ሮ ጥሩማር አባተን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አድርገዋል፡፡

አሁን አመራር አባሉ በመንግስት የተሾሙለት ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ፣ ባለፈው ረቡዕ መስከረም 26 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ይፋ በተደረገበት ወቅት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበሩ ዶክተር ዐብዱልቃድር አደምን ለአዲስ አበባ ካቢኔ ሹመት እጩ ቢያደርጋቸውም ሳይቀበለው መቅረቱ ተነግሮ ነበር፡፡

ሆኖም ፓርቲው የጠቅላይ ሚኒትሩን ንግግር ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ብልፅግና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ያለውን ፍላጎት በማድነቅ፣ ከአፈፃፀም ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከብልፅግና ጋር ውይይት ማድረጉን አሳውቆ ነበር፡፡

በተደረገው ውይይትም በአ/አ ካቢኔ ውስጥ እንዲሳተፉ በተጠየቁት የፓርቲው ሊቀመንበር ምትክ ሌላ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር እንዲሳተፉ ከብልፅግና ጋር ስምምነት መደረሱን አስታውሶ፣ ፓርቲውን ወክለው በአዲስ አበባ ካቢኔ አባል እንዲሆኑ የተመረጡት የነእፓ አመራር ለብልፅግና እንዳሳወቀ በመግለጫው ጠቅሷል።

ይሁን እንጂ ነእፓ መርጦ የላካቸው የፓርቲው ተወካይ በካቢኔው ሳይካተቱ መቅረታቸውን በመግለጽ፣ ሆኖም ጉዳዩን በተመለከተ ከብልፅግና የተሰጠው ማብራሪያ እንደሌለ በመግለጽ፣ ፓርቲው ሀገርን በጋራ ለማገልገል ተፎካካሪዎች በመንግስት ስልጣን እንዲሳተፉ በብልፅግና የተሰጠው እድል በሀገሪቱ የመንግስት ታሪክ አዲስ አሰራር በመሆኑ ከገዢው ፓርቲ ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጦ ነበር፡፡

ገዢው ፓርቲ ብልጽግና አዲስ በመሠረተው መንግስት በሚኒስትርነት ደረጃ ከኢዜማ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን፣ ከኦነግ አቶ ቀጀላ መርዳሳን እንዲሁም ከአብን አቶ በለጠ ሞላን ማካተቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img