የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ከኤርትራ ጋር የሚዋሰነው የትግራይ ክልል ሰሜናዊ ክፍል ለእርዳታ ተደራሽ መሆን አለመቻሉን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ቢሮው በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት 75 በመቶ ያህል አካባቢዎች ለእርዳታ ተደራሽ ቢደረጉም፤ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስነው ሰሜናዊ ክፍል፣ በምዕራብ እና በሰሜን ምዕራብ በኩል የፀጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ስላልሆነ እስካሁን እርዳታ ለመስጠት አልተቻለም ነው ያለው፡፡
ኦቻ ከመስከረም 29 እስከ 24፣ 2014 ድረስ የሰበሰበውን መረጃ ትላንት ይፋ ባደረገበት ሪፖርት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚከሰተውን አስቀድሞ ለመገመት አዳጋች እየሆነ እንደመጣም አመልክቷል፡፡
በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት እንደጨመረ እና ጦርነቱ ወደ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች ከተስፋፋ ወዲህ ድጋፍ የሚጠብቁ ሰዎች ቁጥር እንደናረ ገልጿል።
በአፋር ክልል በኩል ከሰመራ ወደ አቤላ ከዚያም ወደ መቀለ የሚወስደው መንገድ ብቻ ለእርዳታ ክፍት መደረጉ ሂደቱን እንዳስተጓጎለ ያመለከተው ኦቻ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች አሁንም ድረስ ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች ስላሉ እርዳታ ለማቅረብ ፈተና እንደገጠመው አስታውቋል።
በሌላ በኩል ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በትግራይ የመሠረታዊ አቅርቦቶች ዋጋ በእጅጉ መናሩንም ቢሮው በሪፖርቱ ያመለከተ ሲሆን፣ በክልሉ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ እጥረት ፈታኝ ሆኗል ነው ያለው፡፡ በተለይም ከሰኔ ወዲህ ሲቪል ሠራተኞች እና ሌሎችም ተቀጣሪዎች ደሞዛቸው ስለተቋረጠ መሠረታዊ አቅርቦት ለማሟላት ተቸግረዋል ብሏል።
በተጨማሪም ሪፖርቱ በትግራይ ክልል ያለውን የሕክምና እና ተዛማጅ ጉዳዮች በማንሳት፣ በመቐለው አይደር ሆስፒታል ውስጥ አንድ ሕጻንን ጨምሮ 18 ሰዎች ሄሞዲያሊሲስ ካቲተር በማጣታቸው መሞታቸውንም ያሳያል።
በሌላ በኩል በአጎራባቾቹ የአማራ እና አፋር ክልሎችም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውንም ሪፖርት የጠቀሰ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ከሰሜን ጎንደር፣ ከማዕከላዊ ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከደቡብ ወሎ እና ከአዊ ዞኖች የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አፋጣኝ እርዳታ ያሻቸዋል ሲልም አስፍሯል፡፡