Thursday, November 21, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያ አመላልሷል የሚለውን የሲኤንኤን ዘገባ ውድቅ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 28፣ 2014 ― በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ባለፈው ዓመት የትግራይ ጦርነት በጀመረ ሰሞን ከአዲስ አበባ የኤርትራ ከተሞች ወደሆኑት አስመራ እና ምጽዋ ከተሞች የጦር መሳሪያ አመላልሷል በሚል በአሜሪካው ሲኤንኤን የቀረበውን ዘገባ ውድቅ አድርጓል፡፡

አየር መንገዱ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ በውል በሚያውቀው ሁኔታ ወደ የትኞቹም መዳረሻዎቹ የትኞቹንም አውሮፕላኖቹ ለጦር መሳሪያ ማጓጓዣነት አልዋሉም ብሏል፡፡

ሲኤንኤን በዘገባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያዎቹን ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ምጽዋ አጓጎዟል ያለው በ2013 ጥቅምት ወር የመጨረሻ ቀን ጀምሮ ሲሆን፣ ለዚሁ አስረጂ ነው ያለውን ኅዳር 3 እና 4፣ 2013 ተፈጽሟል የተባለውን የጭነት ሰነድ አያይዟል፡፡

ነገር ግን አየር መንገዱ በዘገባው ማስረጃ ተብለው የተጠቀሱት ሰነዶች በግለጽ እንደሚያሳዩት ተጓጓዙ የተባሉት ነገሮች የዓለም አቀፉን የአየር ትራንስፖርት ማሕበር (አይኤቲኤ) ደንብ የተከተሉ ምግብ ነክ እቃዎች መሆናቸውን አሳውቋል፡፡ አየር መንገዱ በዘገባው የተያያዙ ምስሎችንም እንደማያውቃቸው ነው በመግለጫው ያመለከተው፡፡

ሲኤንኤን የአየር መንገዱ ጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላኖች በአዲስ አበባ፣ አሥመራ እና ምጽዋ ከተሞች መካከል ቢያንስ የጦር መሳሪዎችን አጓጉዘዋል ያለው ቢያንስ ለ6 ጊዜያት ነው፡፡ ሆኖም ሚዲያው ተጓጉዟል ላለው መሳሪያ አየር መንገዱ የተጠቀመው የመንገደኞች አውሮፕላኖችን መሆኑን አስረጂ አላገኘሁም ብሎ ነበር፡፡

የአሜሪካው ሲኤንኤን ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያ አጓጉዟል በሚል ዘገባ ይዞ መውጣቱን ተከትሎ ጉዳዩ መነጋጋሪያ ሆኗል፡፡ ዘገባውን ያስነበበው ሲኤንኤን በተከታይ ዘገባው የጆ ባደን አስተዳደር አየር መንገዱ የጦር መሳሪያ አጓጉዟል የመባሉ ነገር አሳሳቢ ነው ማለቱን አክሏል፡፡ ድርጊቱ ተፈጽሞ ከሆነም ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ሕግጋትን እና በዓለም ላይ የመንገደኞች አውሮፕላን ደህንነትን አደጋ ላይ እንደሚጥል አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደነገሩትም ነው የገለጸው፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲኤንኤንን ዘገባ ውድቅ ባደረገበት መግለጫው አንድም የአየር መንገዱ ባልደረባ በብሔሩ ምክንያት እግድ ወይም ውል የመቋረጥ እንዳልገጠመው በማሳወቅ፣ ይህንኑ ከተቋሙ የሰው ኃይል አስተዳደር ማረጋገጥ ይቻላል ብሏል፡፡ አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም የትግራይ ተወላጆችን በግዳጅ የሥራ እረፍት እንዲወስዱ አድርጓል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡበት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በአገልግሎቱ በርካታ አድናቆት የሚቸረው ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በቢዝነስ ትራቭሌር አዋርድ የ2020 የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በመባል የተሸለመ ነው፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከቀናት በፊት ፍላይት ግሎባል በለንደን ባዘጋጀው የአየር መንገዶች የቢዝነስ ስትራቴጂ ሽልማት ላይ በአየር እቃ ጭነት አገልግሎት አመራር ዘርፍ መሸለማቸው መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img