Thursday, November 21, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትግራይ ጦርነት መጀመሪያ ሰሞን ወደ አስመራ እና ምጽዋ ጦር መሳሪያ ማመላለሱ ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ መስከረም 27፣ 2014 ― በአፍሪካ ግዙፉ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት የትግራይ ጦርነት በጀመረ ሰሞን ከአዲስ አበባ የኤርትራ ከተሞች ወደሆኑት አስመራ እና ምጽዋ የጦር መሳሪያ ማመላለሱን ሲኤንኤን በምርመራ ዘገባዬ ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡

ዘገባው አየር መንገዱ የጦር መሳሪያዎቹን ወደ ተጠቀሱት የኤርትራ ከተሞች አመላልሷል ያለው በ2013 በጥቅምት ወር የመጨረሻ ቀን ጀምሮ ነው፡፡

የፈዴራል መንግስት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ሕወሃት ጥቃት ማድረሱን በመግለጽ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ ማስከበር እርምጃ እንዲጀምር ትእዛዝ መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይፋ ያደረጉት ጥቅምት 24፣ 2013 እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ሲኤንኤን ይዞት በወጣው ዘገባ ከአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አስመራ መዳረሻው መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ አያይዞ የወጣ ሲሆን፣ ጭነቱ የተፈጸመበት ቀን ከጥቅምት 30፣ 2013 ጀምሮ መሆኑን በመግለጽ ለዚሁ አስረጂ ኅዳር 3 እና 4፣ 2013 ተፈጽሟል የተባለውን ጭነት ሰነድ አያይዟል፡፡

ሲኤንኤን የአየር መንገዱ ጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላኖች በአዲስ አበባ፣ አሥመራ እና ምጽዋ ከተሞች መካከል ቢያንስ 6 ጊዜ ጦር መሳሪያዎችን ስለማጓጓዛቸው ሰነድ፣ ፎቶግራፍ ማስረጃዎች እንዲሁም የአሁን እና የቀድሞ የአየር መንገዱን ሠራተኞች በዓይን ምስክርነት ጠቅሶ ማረጋገጡን የጠቀሰ ቢሆንም፣ የመንገደኞች አውሮፕላኖች ለዚህ ተግባር ስለመዋላቸው ግን ማስረጃ አላገኘሁም ነው ያለው ፡፡

በዘገባው የጦር መሳሪያ አመላልሷል የተባለው አየር መንገዱ በበኩሉ፣ እስከማውቀው ድረስ አውሮፕላኖቼ ጦር መሳሪያ ለማጓጓዝ አልዋሉም በማለት ማስተባበሉ ሠፍሯል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ የጦር መሣሪያዎችን እና ወታደሮችን ወደ ትግራይ ክልል አጓጉዟል በሚል በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች መረጃ ቢሰራጭበትም፣ መረጃዎቹን ‹‹መሠረተ ቢስ›› ሲል አጣጥሏቸው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፉን የአየር ትራንስፖርት ማሕበርን (አይኤቲኤ) የአደገኛ ቁሶች ሕጎችን ጨምሮ ክልላዊና ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ደንቦችን በጥብቅ እንደሚከተልም በወቅቱ አስታውቋል።

ባለው የደህንነት ጥበቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታወቅ የገለጸው አየር መንገዱ፤ ‹‹መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይህ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦች የአየር መንገዱን ከፍተኛ ዝና ለማጠልሸት እየሠሩ ነው›› ሲልም ወቅሶ ነበር፡፡  

በአገልግሎቱ በበርካታ አድናቆት የሚዥጎደጎድለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በቢዝነስ ትራቭሌር አዋርድ የ2020 የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በመባል እንደተሸለመ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img