Monday, October 7, 2024
spot_img

በትግራይ በቀን ከ3 እስከ 4 ሰዎች በረሐብ እየሞቱ ነው ሲሉ የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ

ባለፈው ዓመት በትግራይ ጦርነት ከተከሰተ በኋላ የፌደራል መንግሥት የክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅርን ሕገ ወጥ ብሎ ቢያፈርሰውም አሁንም የጤና ቢሮ ኃላፊ እንደሆኑ የሚናገሩት ዶ/ር ሐጎስ ጎደፋይ ‹‹በቀን በየሆስፒታሉ ከ3 እስከ 4 ሰዎች በረሐብ እየሞቱ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ሐጎስ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ አስቸኳይ የእርዳታ አቅርቦት እንዲደርስ ካልተደረገ በ1977 የነበረው ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል በረሃብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በርካታ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሐጎስ ጎደፋይ፣ በክልሉ የመገናኛ ዘዴዎች ችግር በመኖሩ የረሃቡን መጠን ሙሉ በሙሉ ለማወቅ አዳጋች እንዳደረገው አመልክተዋል፡፡

ኃላፊው በማዕከላዊ ዞን አካባቢዎች ተምቤን፣ አድዋና አክሱም፣ ዛና – የሠሜን ምዕራብ አካባቢዎች፣ በራያ እንዲሁም እንዳሞኾኒ፣ በደቡብ ምሥራቅ ደረጃው ቢለያይም በርካታ ወረዳዎች ‹‹አደጋ ላይ›› መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ አካባቢዎች ከዚህ በፊትም በረሃብ የሚጠቁ እንደነበሩ ኃላፊው አክለው አመልክተዋል።
ዶ/ር ሐጎስ በክልሉ ያለውን ሁኔታ ለመመልከት በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው እንደነበር ገልፀው፣ በተለይም በማዕከላዊ ዞን፣ ራያ አካባቢ እንዲሁም ተንቤን ያለውን ሁኔታ መታዘባቸውን ይናገራሉ።

‹‹የረሃብ ሁኔታው እየባሰበት ነው። በተለይም በሕጻናት፣ በሚያጠቡ እናቶችና በነፍሰ ጡሮች ላይ የሚታው ችግር ሰፊ ነው›› ብለዋል።

ያለውን ሁኔታ በተመለከተም በዓለም ደረጃ ባለው የምግብ እጥረት መለኪያ ሲለካ ‹‹25 በመቶ ደርሷል። አንድ አገር 15 በመቶ ከደረሰ አደጋ ላይ እንዳለች ታውቆ የምግብ እርዳታ ለማደል እቅድ ይወጣል። አሁን እዚህ 25 በመቶ ደርሷል›› ሲሉ ተናግረዋል።

የጤና ኬላዎች የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ቢጠበቅባቸውም ይህን እያደረጉ አለመሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሐጎስ፣ በረሃብ የተጎዱ ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም ቢመጡም በሆስፒታሎች በቂ የምግብ አቅርቦት ባለመኖሩ ችግሩ የበለጠ ፈታኝ መሆኑን ያስረዳሉ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊም ‹‹ጥሬ ገንዘብ የለም። የጤና አገልግሎት እጥረትም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው። አሁን በነጻ ነው እየሰራን ያለነው።›› ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በተመለከተ በቅርብ ጊዜያት ባወጣቸው መግለጫዎች ‹‹በአስርት ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ አስከፊው የረሃብ ሁኔታ›› ሲል የገለጸውን ክስተት ለመቀልበስ ከተፈለገ 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የአስቸኳይ እርዳታ ሊቀርብላቸው ይገባል ብሏል፡፡ ድርጅቱ ቀደም ሲል 400 ሺሕ የሚሆን ሕዝብ በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሚገኝም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከነሐሴ 16 ጀምሮ አንድም እርዳታ የጫነ መኪና ወደ ትግራይ አልደረሰም ሲል ቅሬታ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በየቀኑም በ100 መኪኖች የተጫነ የእርዳታ አቅርቦት ለክልሉ እንደሚያስፈል ሲገልጽ ነበር፡፡

መንግሥት በበኩሉ ከቀናት በፊት በክልሉ ደርሰዋል ያላቸውን 152 የጭነት መኪኖችን ጨምሮ 500 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባታቸውን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የእርዳታ አቅርቦቱን ለማፋጠን የፍተሻ የደኅንነት ኬላዎች ቁጥርን ወደ ሁለት መቀነሱን አሳውቆ ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img