አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ መስከረም 25፣ 2014 ― ባለፈው ሳምንት ሐሙስ መስከረም 20 የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የአገሪቱን ሉአላዊነትን የሚጥስና ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚሆኑ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ያላቸውን ሰባት የተመድ ሠራተኞች በ72 ሰዓታት የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡
ይኸው ከይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ ሠራተኞቹ የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው መውጣታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ኢትዮጵያ ውሳኔዋን የማትቀለብስ ከሆነ ቆራጥ ምላሽ ከመስጠት ወደኋላ እንደማትል ያስጠነቀቀችው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በትላንትናው እለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንኑ አረጋግጠው፣ ሠራተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የነፍስ አድን ሥራቸውን እንዲቀጥሉ መፈቀድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ኔድ ፕራይስ ይህን ቢሉም፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ መንግስት ከተመድ ጋር በትብብር የሰብአዊ አቅርቦቱን እንዲቀጥል በተባረሩት ሠራተኞች ቦታ ሌሎችን እንዲተካ ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት ግለሰቦች በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች ናቸው። ከግለሰቦቹ መካከል አምስቱ በድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ)፣ አንደኛዋ በድርጅቱ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዲሁም አንደኛው የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ውስጥ በኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ናቸው።
ለሠራተኞቹ መባረር በመንግስት ከቀረቡት ምክንያቶች መካከል ለትግራይ ሕዝብ የመጣ እርዳታ ለሕወሓት መስጠት፣ በፀጥታ ጉዳይ የተደረጉ ስምምነቶች መጣስ፣ የግንኙነት መሳሪያዎችን ለሕወሀት ማቀበል፣ የእርዳታ እህል ጭነው ትግራይ የገቡና ሕወሀት ለወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚጠቀምባቸውን 400 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመመለስ ተደጋጋሚ እንቅፋት መፍጠር እንዲሁም የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት የሚል ይገኝበታል፡
በወቅቱ የተላለፈውን የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ፣ ኢትዮጵያ የተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ መወሰኗ ‹‹አስደንግጦኛል›› ሲሉ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ጉቴሬዝ በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተነጋግረዋል፡፡
ጉቴሬዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ፣ የዲፕሎማቶችን ሕጋዊ ከለላ ማንሳት የሚቻለው፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ላይ ሳይሆን፣ የመንግስታት ዲፕሎማቶች በሆኑት ላይ ብቻ ነው የሚል መከራከሪያ አንስተዋል። የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ፈርሐን ሐቅ በበኩላቸው ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው በአገራት ግንኙነት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ውሳኔ ተከትሎ አሜሪካ እና ፈረንሳይን ጨምሮ ሌሎችም አገራት ባቀረቡት ጥያቄ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ዐርብ መስከረም 21 በዝግ መክሯል፡፡
በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የተወሰኑ አገራት ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ግፊት ቢያደርጉም፣ ቻይና እና ሩሲያ ጉዳዩን በዝርዝር ማጤን እንደሚያስፈልግ ማንሳታቸው ሲነገር፣ አክለውም የትግራዩ ግጭት የውስጥ ጉዳይ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡