Sunday, November 24, 2024
spot_img

የኢዜማ መሥራች አባሉ ከፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ማግሥት ፓርቲውን መልቀቃቸውን አሳወቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ መስከረም 24፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሥራች አባል የሆኑት አቶ ዘላለም ወርቃለማሁ ፓርቲው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ባደረገ ማግሥት መልቀቃቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈው ባሰራጩት አጭር መልእክት አሳውቀዋል።

ከዚህ ቀደም በኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ያገለገሉትና ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ ወረዳ 10 እጩ የነበሩት አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ፣ ፓርቲውን ለምን እንደለቀቁ ይፋ ያደረጉት ነገር የለም። ነገር ግን ፓርቲው ቅዳሜ መስከረም 23 እና እሑድ መስከረም 24 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች በተቃርኖ መቆማቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል።

ከሰሞኑ ከገዢው ብልፅግና ፓርቲ አብረን እንሥራ ጥያቄ እንደቀረበለት ሲነገር የነበረው ኢዜማ፣ በጠቅላላ ጉባዔው ይህንኑ የብልጽግና ጥያቄ አቅርቦ የ536 አባላት ድጋፍ ሲያገኝ፣ 79ኙ ተቃውመውት፣ በ25 ድምፀ ተዓቅቦ የኢዜማ አባላት የሆኑ ሰዎች በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተሰጣቸውን/የሚሰጣቸውን ሹመት እንዲቀበሉ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉን አሳውቋል።

ውሳኔውን በተመለከተ በጉባዔው ላይ የኢዜማ መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) «ብልፅግና ፓርቲ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለን ወደ ተግባር ስንሄድ ብዙ ክርክር ይኖራል፣ አብሮ መሥራት ከተቻለ እነሱ ውስጥ ካሉ ከጥቂቶቹም ጋር ቢኾን በመተባበር ሰንኮፉን መንቀል ይቻላል፤ አሁን ላይ ያለውን ችግር ለማስተካከል ጊዜ ይፈጃል፣ ሁኔታውን ዓይተን የማይስተካከል ከሆነ ለቀን እንወጣለን» ብለዋል።

ኢዜማ ከከፍተኛ የፌዴራል ቦታዎች ጀምሮ እስከ ወረዳ መዋቅር ድረስ ባሉት በመግባት እንደሚሰራም መሪው አክለው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረጉት ካቢኔ፣ የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ አቶ ግርማ ሰይፉን ሾመው ነበር። ሆኖም ከንቲባዋ ሹመቱን ቢሰጡም አቶ ግርማ ሰይፉ በወቅቱ የካቢኔ አባላት ቃለ መሐላ በፈጸሙበት ወቅት ሳይገኙ ቀርተዋል። በወቅቱ ለአቶ ግርማ አለመገኘት ብልጽግና ቀድሞ ይህንኑ መረጃ አለማሳወቁ እንደ ምክንያት ተጠቅሶ ነበር።

ኢዜማ በተመሳሳይ ሌላ አባሉ በደቡብ ክልል ካቢኔ ውስጥ ሹመት ተሰጥቷቸዋል።

በግንቦት ወር 2011 የተመሠተው ኢዜማ በአገራዊ ምርጫ ወቅት ከገዢው ብልጽግና በመከተል 1 ሺሕ 385 ዕጩዎችን ያቀረበ ቢሆንም፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወንበር ካገኙ አራት እጩዎቹ ውጭ በአዲስ አበባ ከተማ የተወዳደሩት መሪውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ መቀመጫ ሳያገኝ ቀርቷል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ ከምሥረታው ጀምሮ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ ጋር የበዛ ቅርርብ አለው በሚል በአንዳንዶች ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img