አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 22፣ 2014 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ መንግስት ከትላንት በስትያ ሐሙስ መስከረም 20 በአስቸኳይ አገር ለቃችሁ ውጡ ያላቸው ሠራተኞቻቸውን ጉዳይ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋጋራቸው ተሰምቷል፡፡
ጉቴሬዝ በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የተመድ ሠራተኞችን የማባረር ሕጋዊ ሥልጣን የለውም የሚል መከራከሪያ ማቅረባቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ ፈርሐን ሐቅን ጠቅሶ ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
እንደ ጉቴሬዝ ከሆነ የዲፕሎማቶችን ሕጋዊ ከለላ ማንሳት የሚቻለው፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ላይ ሳይሆን፣ የመንግስታት ዲፕሎማቶች በሆኑት ላይ ብቻ ነው። ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው ደግሞ በአገራት ግንኙነት መሆኑን ያመለከቱት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹እኛ አገር አይደለንም›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡
የመንግስታቱን ድርጅት ጨምሮ በተለያዩ አገራት የተለያዩ ምላሾች እያስተናገደ በሚገኘው ውሳኔ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገር ለቃችው ውጡ የተባሉት ሰባት ሠራተኞች በኢትዮጵያ ቆይታቸው ፈጽመዋቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች ይፋ አድርጓል፡፡
ለሠራተኞቹ መባረር በመንግስት ከቀረቡት ምክንያቶች መካከል ለትግራይ ሕዝብ የመጣ እርዳታ ለሕወሓት መስጠት፣ በፀጥታ ጉዳይ የተደረጉ ስምምነቶች መጣስ፣ የግንኙነት መሳሪያዎችን ለህወሀት ማቀበል ወይም መስጠት፣ የእርዳታ እህል ጭነው ትግራይ የገቡና ህወሀት ለወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚጠቀምባቸውን 400 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን ለመመለስ ተደጋጋሚ እንቅፋት መፍጠር እና የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨት የሚል ይገኝበታል፡
ሰባቱ የተመድ ሠራተኞች የኢትዮጵያን ግዛት ለቀው ይውጡ የሚለውን የመንግስት ውሳኔ ተከትሎ ምላሽ ከሰጡት አገራት መካከል የሆነችው አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊዋ አንቶንዮ ብሊንክን በኩል ኢትዮጵያ ውሳኔውን እንድትቀለብስ ማሳሰቧ አይዘነጋም፡፡ ብሊንክን ኢትዮጵያ ውሳኔዋን የማትቀለብስ ከሆነ አገራቸው ቆራጥ ምላሽ ከመስጠት ወደኋላ እንደማትልም አስጠንቅቀው ነበር፡፡