አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 21፣ 2014 ― በነገው እለት ቅዳሜ መስከረም 22 በአዲስ አበባ፣ ከነገ በስትያ መስከረም 23 ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ በሚከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የቱለማ አባገዳ የእሬቻ አከባበር አስተባባሪ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ገልጸዋል፡፡
አባ ገዳ ጎበና ሆላ በዘንድሮው የኢሬቻ በዐል ‹‹ሳር ብቻ ይዘን ነው ወደ ወንዝ የምንወርደው፤ ፖለቲካው ለሌላ ጊዜ ይቆየን›› እንዳሉት ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
አባ ገዳው ለበዓሉ የሚመጡ ታዳሚዎች ወደ መልካው ሲሄዱ የኢሬቻ በዓል ትውፊቶችን ከሚገልፁ ነገሮች ውጪ ሌላ ነገር ይዘው እንዳይሄዱም መልዕክት አስተላለፈዋል። ‹‹ኦሮሞ የራሱ ትውፊት እና ባህል አለው፤ ወጣቶች፣ አዛውንቶች፣ አባገዳዎች፣ አደ ሲንቄዎች፣ ምን ምን ይዘው እንደሚወጡ ያውቁታል። ወደ ወንዙ የምንመጣው እርጥብ ሳር ብቻ ይዘን ነው›› ብለዋል።
አክለውም ‹‹ኢሬቻ ፖለቲካ መሆን የለበትም፤ እኛ የአባ ገዳ ባንዲራ እንኳ ይዘው እንዲመጡ አናስገድድም፤ ነገር ግን ይህን ባንዲራ ይዛችሁ ኑ፤ ወይ ደግሞ ይህንን አትያዙ ማለት ይጨንቀናል፤ እንደዚያ ካልን ከፖለቲካ ጋር ይቀላቀላል። እንደዚህ እንዳይሆን እንደ ትውፊታችን እርጥብ ሳር ብቻ ይዘን እንምጣ›› ብለዋል።
አባ ገዳ ጎበና ሆላ በዓሉን በሰላም ለማክበር እንዲቻል የተለያዩ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን በመግለጽ፣ ‹‹የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓልን የምናከብረው በሁለት ትልልቅ ችግሮች ውስጥ እያለን ነው›› በማለት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በአገሪቱ ያለው የሰላም እጦትን ጠቅሰዋል።
በዓሉን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ቢሾፍቱ የሚመጡ ተሳታፊዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
አባ ገዳ ጎበና አክለውም በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይን በተመለከተም ኅብረተሰቡ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
በዘንድሮው ኢሬቻ በዓል በሁለቱም ከተሞች የኢሬቻ በዓልን ለማክበር በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል፡፡