አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ መስከረም 20፣ 2014 ― በዓለም ሕፃናት አድን ድርጅት ጽሕፈት ቤት (ዩኒሴፍ) ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ እና በኢትዮጵያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ህገ ወጥ ሥራ ሲሠሩ የተገኙ ናቸው ያላቸው የውጭ ሃገር ዜጎች በ72 ሰዓታት ውስጥ እንዲወጡ መታዘዙን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከሃገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ከተሰጠባቸው አራት የውጭ ሃገራት ዜጎች መካከል ሚስ አደል ኮድር በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ይገኙበታል፡፡መግለጫው መንግስት ከድርጅቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደገና ለማጤን እንደሚገደድም አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ከሃገር ውስጥ እንዲወጡ ከተወሰነባቸው ግለሰቦች መካከል በድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተጠባባቂ ምክትል አስተባባሪ የሆኑት ሚስ ጋዳ ኢል ታሂር ሙዳዊ ይገኙበታል፡፡በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ አገልግሎት አስተባባሪና ቋሚ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የሰላምና ልማት አስተባባሪ የሆኑት ሚስተር ኪዌሲ ሳንስክሎቴ ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም ሚስተር ሳኢድ ሞሐሙድ ሔርሲ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ኃላፊ እንዲሁም ሚስተር ግራንት ሊቴ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ አገልግሎት ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የሰብዓዊ ድጋፍ ምክትል አስተባባሪ ተካተዋል።