Thursday, November 21, 2024
spot_img

የኢዜማ ጠቅላላ ጉባዔ የምርጫ ቦርድን ትዕዛዝ ለማስፈጸም አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ መስከረም 20፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ጠቅላላ ጉባዔ፤ የመጀመሪያ አስቸኳይ ስብሰባውን በመጪው ቅዳሜ እና እሑድ ሊያካሄድ መሆኑ ተነግሯል።

የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባውን የሚያካሄደው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲው በመተዳደሪያ ደንብ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ በመወሰኑ መሆኑን የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ነግረውኛል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።

በምርጫ ቦርድ የጊዜ ገደብ መሰረት ኢዜማ የመተዳደሪያ ደንቡን ማሻሻል የሚጠበቅበት፤ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ባሉት የሶስት ወራት ጊዜ እንደሆነ አቶ ናትናኤል ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት መተዳደሪያ ደንብ የማሻሻል ስልጣን ያለው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ በመሆኑ፣ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን አስረድተዋል።

በአዜማ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፓርቲው ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤ፤ መደበኛ ስብሰባ የሚያካሄደው በየሶስት ዓመቱ ነው። ጠቅላላ ጉባኤውን አስቸኳይ ስብሰባ እንዲቀመጥ ያስገደደው የምርጫ ቦርድ ውሳኔ፤ ኢዜማ በመተዳደሪያ ደንቡ አራት ጉዳዮችን እንዲያሟላ ያዝዛል።የመጀመሪያው ጉዳይ የፓርቲው አባላት በሀገር አቀፍ እና በሌሎች ምርጫዎች የሚታጩበት ስርዓትን ነው።

በ2011 የጸደቀው አዲሱ የምርጫ አዋጅ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸውን ለምርጫ የሚያጩበት ስርዓት ምን እንደሚመስል በመተዳደሪያ ደንባቸው እንዲያካተቱ ያስገድዳል። ኢዜማ በምርጫ ቦርድ እንዲያሟላ የተጠየቀው ሁለተኛ ጉዳይ፤ በፖለቲካ ፓርቲው ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች የሚፈቱበትን ስርዓት ነው። ማንኛውም አባል እኩል ድምጽ ያለው መሆኑን የሚገልጽ ድንጋጌ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ እንዲካተት ማድረግ በሶስተኛነት የተቀመጠ ጉዳይ ነው።

ኢዜማ በመተዳደሪያ ደንቡ እንዲነግግ የሚጠበቅበት የመጨረሻው ጉዳይ ደግሞ የፓርቲው አመራሮች እና ኃላፊዎች አመራረጥ ግልጽ፣ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሁም በሚስጥር የሚሰጥ መሆኑን በግልጽ የሚያስቀምጥ አንቀጽ ነው። ፓርቲው እነዚህን እና ሌሎች በከፊል ያላሟላቸውን ጉዳዮች በመተዳደሪያ ደንቡ “አሟልቶ እንዲያቀርብ” መታዘዙን የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልጸዋል።

በአስቸኳይ ስብሰባው ከመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል በተጨማሪ “በተያያዥነት የሚሰሩ ስራዎች አሉ” የሚሉት ናትናኤል፤ ጉባኤው በሌሎች አጀንዳዎች ላይም እንደሚወያይ ጠቁመዋል። የኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ፤ በፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚቀርበውን የምርጫ 2013 አጠቃላይ ሪፖርትን እና የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ ካደመጠ በኋላ ምክረ ሃሳቡን ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ገዢው የብልፅግና ፓርቲ በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ ቦታዎች ላይ የኢዜማ አባላትን ለመሾም ያቀረበው ጥያቄ ላይ ጉባኤው ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አስረድተዋል።

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መስከረም 18 በተካሄደው የአዲስ ምክር ቤት የምስረታ ስብስባ ላይ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን በኃላፊነት እንዲመሩ በከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መሾማቸው ይታወሳል።

የአቶ ግርማ ሰይፉ ሹመት ለፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ እንደሚታይ ኃላፊው ተናግረዋል። ከአቶ ግርማ በተጨማሪ ሌሎች የፓርቲው አመራሮች ለመንግስት የስራ ኃላፊነት ቦታ ታጭተው እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ናትናኤል፣ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ከመስጠት እንደተቆጠቡም በዘገባው ተጠቅሷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img